ታሕሳስ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ብቻ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታን ሙሉ ለሙሉ ከታለመለት አላማ ውጪ ሲጠቀሙ የተገኙ 187 የህንፃ ባለቤቶች እያንዳንዳቸው 100 ሺሕ ብር እንዲቀጡ መደረጉን የአዲስ አበባ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክበበው ሚደቅሳ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ በቅርቡ ፀድቆ ወደ ሥራ በገባው የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት አሰጣጥ ደንብ መሰረት ጥፋተኛ ሆነው የተገኙት የሕንፃ ባለቤቶች የተጣለባቸውን የ100 ሺሕ ብር ቅጣት ከፍለዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን የተሸከርካሪ ማቆሚያ ወይም ፓርኪንግ አገልግሎት ፈቃድ እንዲወስዱ መደረጉን ተናግረዋል።
ቦታውን ሙሉ ለሙሉ ወደ እቃ ማስቀመጫ እና ለንግድ አገልግሎት የማዋል ሥራ ሲሰራ እንደነበር ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ የተሽከርካሪ ማቆሚያውን በከፊል ለሌላ አላማ ያዋሉ አካላት ላይ ደግሞ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን አስረድተዋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አክለውም፤ ሕንጻዎች ከዲዛይናቸው ጀምሮ የግንባታ ፈቃድ ሲሰጣቸው የራሱ የሆነ አላማ እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡
ባለስልጣኑ በከተማዋ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል፤ የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የትራፊክ ፍሰቱ እንዲሳለጥ የሚያደርጉ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሰረት ሕጉን ተግባራዊ በማያደርጉ አካላት ላይ አሁንም ቅጣቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹም ሲሆን፤ እስካሁን በስፋት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሰራ መቆየቱንም ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የተሸከርካሪ ማቆሚያ ስፍራዎችን ማስተዳደር የሚያስችለውን፤ የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት አሰጣጥ ደንብ ቁጥር 165/2016 በከተማ አስተዳደሩ ጸድቆ በሥራ ላይ መዋሉ ይታወሳል፡፡
በዚህም ደንብ መሰረት ሕጉን በተላለፉ አካላት ላይ ከገንዘብ ቅጣት ጀምሮ የፍርድ ቤት ክስና የንግድ ፈቃድ ስረዛ ድረስ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተመላክቷል፡፡