መጋቢት 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ6 ወራት ውስጥ በተደረገው የቁጥጥር ሥራ የተለያዩ እርምጃ የተወሰደባቸው ከ132 ሺሕ በላይ ነጋዴዎች ከሥራ እንዲታገዱ መደረጉ ይታወሳል፡፡

አሐዱ "እርምጃ ከተወሰደባቸው ነጋዴዎች ምን ያክል ወደ ሕጋዊ መንገድ እንዲመለሱ ተደርጓል?" ሲል የክልሉን ንግድ ቢሮ ጠይቋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ የቁጥጥር ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ቆጲሳ በምላሻቸው፤ በተለያዩ ሕገ-ወጥ ንግድ ተስማርተው ሲሰሩ በነበሩ 132 ሺሕ በላይ ነጋዴዎች መካካል 127 ሺሕ የሚጠጉት ወደ ሕጋዊ መንገድ እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ከጽሁፍ ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ በሕግ ተጠያቂ እስከማድረግ ድረስ እርምጃ እንደተወሰደባቸውም ገልጸዋል፡፡

አክለውም 5 ሺሕ 347 የሚሆኑት ነጋዴዎች ደግሞ በሂደት ላይ መሆኑን አንስተው ያለ ንግድ ፈቃድ መስራት፣ ያለማደስ ፤ ዋጋ ሳይለጥፉ መሸጥ፣ ጊዜ ያለፈባቸውን ምርቶች በገበያ በማቅረብ እንዲሁም ዋጋ ጨምሮ በመሸጥ የታዩ ክፍተቶች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

በሕገ-ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ ክትትል በማድረግ እርምጃዎች እንደሚቀጥል አንስተው፤ እንደዚህ አይነት ድርጊቶችን ቁጥጥር ለማድረግ ማንኛውም ማህበረሰብ ትብብር ሊያደርግ ይገባልም ብለዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ