ታሕሳስ 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ መንግሥትና ሕዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው፤ ከኮሪደር ልማት የፍርስራሽ ግምት ለግል ጥቅማቸው ሊያውሉ የሞከሩ 3 አመራሮች በከተማው የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እያካሄደው ባለው የኮሪደር ልማት ሥራ ከተማዋን የሚመጥኑ ሰፋፊ የመንገድ መሠረት ልማቶችን እና ግዙፍ ተሻጋሪ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ መሆኑን ባወጣው መግለጫ አንስቷል።
በዚህም መተለይ በየካ ክፍለ ከተማ በካዛንችስ የኮሪደር ልማት ሥራ ከልማቱ ፍራስራሽ ላይ ለግል ጥቅማቸው ሊያውሉ የነበሩ የወረዳ 06 አመራሮች አስተዳደሩ በዘረጋው የሕዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ በትናንትናው ዕለት በፀጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር በማዋል ተገቢውን እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።
በዚሁ መሠረት በቁጥጥር ሥር የዋሉት አመራሮች፤ በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ 06 ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ራሄል ኃ/ኢየሱስ፣ የወረዳው ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደበበ ጉልማ፣ የወረዳው የፋይናስ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታደለ ግዛቸው መሆናቸውን ገልጿል።
ግለሰቦቹ የኮሪደር ልማትን መነሻ አድርገው የፍራስራሽ ግምትን ለግል ጥቅማቸው ለማዋል በመሞከር ላይ እያሉ፤ የከተማዋ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ እስከ ክፍለ ከተማ ያለውን መዋቅሩን በመጠቀምና ክትትል በማድረግ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ማድረጉን ገልጿል።
የወንጀል ማጣራት ሥራው በሚመለከተው አካል እየተካሄደ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፤ ሌብነትን እና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት የሚደረገው ትግል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡
አክሎም "አስተዳደሩ የከተማዋን ፈተናዎች ባሏት ፀጋዎቿ በማሻገር ሁለንተናዊ ብልፅግናዋን ለማረጋገጥ በሚጥርበት በዚህ ወቅት የኮሪደር ልማትን መነሻ በማድረግ የግል ፍላጎታቸውንና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚሯሯጡ አልጠፉም" ሲልም ገልጿል።
የከተማ አስተዳደሩ "በቀጣይ የተጀመሩ ልማቶችንን በማሳለጥ ሌብነት ላይ የሚደረገው ትግል ተጠናክሮ ይቀጥላል" ያለ ሲሆን፤ ሕብረተሰቡም ጥቆማ በመስጠት የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ