ታሕሳስ 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በፌደራል መንግሥት መመለስ የሚገባቸው ዋና ዋና የሠራተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ማስመለስ ከፍተኛ ፈተና እንደሆነበት የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) አስታውቋል።
ኢሠማኮ 20ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሄደ ሲሆን፤ በጉባኤውም ኮንፌዴሬሽኑን ለበርካታ ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩትን አቶ ካሣሁን ፎሎን ለሚቀጥሉት አምስት አመታት እንዲያገለግሉ መርጧል።
በጉባኤውም ከ2012 እስከ 2016 በጀት ዓመት ያለው የ5 ዓመት የኦዲት ኮሚቴ ሪፖርት ቀርቧል።
በሪፖርቱ "ኢሠማኮ በ2011 በጀት ዓመት በአሰሪ እና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ተሳትፎ በማድረግ አዋጁ ለሁሉም የኢትዮጵያ ሠራተኞች እና ማህበራት ጠቃሚ እንዲሆን አስችሏል" ሲሉ የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሣሁን ፎሎ ተናግረዋል።
"ይሁን እንጂ ከዚያ ወዲህ በፌደራል መንግሥት መመለስ የሚገባቸውን ዋና ዋና የሠራተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ማስመለስ ከፍተኛ ፈተና ሆኖበት ይገኛል" ሲሉ ገልጸዋል።
የኢሠማኮ ሥራ አስፈፃሚ በጥያቄዎች ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ሰፊ ውይይት አድርጎበት የነበረ ቢሆንም፤ በወቅቱ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ተግባራዊ ሊደረግ አልቻለም ብለዋል።
በተለይ የዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ጥያቄ እና የግብር ቅነሳ ጥያቄ ዋነኞቹ የሠራተኛው ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች እንደሆኑ የገለጹት ደግሞ፤ የኮንፌዴሬሽኑ የኦዲት ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ኦላኒ ሴቃታ ናቸው።
"ኢትዮጵያ ውስጥ የኑሮ ውድነቱ ጣራ በነካበት ወቅት ከአንድ ሺሕ እስከ ሁለት ሺሕ የሚከፈለው ሠራተኛ በጣም በርካታ ነው፤ ይህም በምኑ በልቶ፣ ለብሶ እና ተከራይቶ እንደሚኖር አጠያያቂ የሚሆን ጉዳይ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም "የተሻለ ደመወዝ ይከፈላቸዋል የሚባሉ ሠራተኞችም ቢሆን፤ ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት በወጣው እና የወቅቱን የገበያ ሁኔታ ባላገናዘበው የገቢ ግብር አዋጅ ስለሚተዳደር አብዛኛው ተመልሶ በግብር ይወሰድበታል" ብለዋል።
"ይህ ደግሞ የተቀጣሪው ማህበረሰብ ክፍል የተረጋጋ እና ተመጣጣኝ የሆነ ኑሮ እንዳይኖር አድርጎታል" ብለዋል። በቀጣይ ጥያቄዎች መልስ እስከሚያገኙ ድረስ በትኩረት እንደሚሰራ ተመላክቷል።
በሌላ በኩል የኢሠማኮ ሥራዎችን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ቢኖሩም፤ ከኮንፌዴሬሽኑ የተደራሽነት ውስንነት ጋር ተያይዞ በርካታ ቅሬታዎች እና ትችቶች ሲነሱ እንደነበር ይታወሳል።
በተለይም ታች ያለው የኢሠማኮ መዋቅር የተጠናከረ፣ የበቃ እና ለሠራተኞች ችግሮች የሚደርስ ባለመሆኑ የተነሳ ሰፊ ችግሮች ሲነሱ መቆየታቸውን የኢሠማኮ የኦዲት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኦላኒ ሴቃታ ተናግረዋል።
ይህን ችግር ለመፍታት በአዲሱ መዋቅር የኢሠማኮ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን ለማጠናከር እና የመፈፀም አቅማቸውን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።
በዚህ መሠረት በደረጃ እንዲለያዩ ተደርጎ በቂ የሰው ሃይል እንዲመደብላቸው እና አስፈላጊ የሥራ መሳሪያዎች እንዲሟሉላቸው ለማድረግ እንደተሞከረ አንስተዋል።
ነገር ግን የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን የመወሰን ስልጣን እና የበጀት አመዳደብ በተመለከተ ኢሠማኮ እና ፌደሬሽኖች በጋር ሊያስቡበት የሚገባ ስለመሆኑ ተመልክቷል።
ኢሠማኮ በአሁኑ ወቅት ስምንት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አሉ የተባ ሲሆን፤ በሁሉም ክልሎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች እንደሚከፈቱ ተገልጿል።
የኮንፌዴሬሽኑን ተቋማዊ አቅም መገንባት ከማንኛውም ዓይነት ጥገኝነት እና ተጋላጭነት የማላቀቅ እንዲሁም የመፈጸም እና የማስፈፀም አቅም ማጎልበትን እንደሚያካትት ተጠቁሟል።
በመንግሥት መመለስ የሚገባቸውን ዋና ዋና የሠራተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ማስመለስ ከፍተኛ ፈተና ሆኗል ሲል ኢሠማኮ ገለጸ
👉 ካሣሁን ፎሎ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ኮንፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ በድጋሚ ተመርጠዋል