ጥር 5/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ 80 በመቶ የሚሆነውን የዘይት አቅርቦት ከውጭ የምታስገባ ሲሆን፤ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ለመተካት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ መኩሪያ ለአሐዱ ገልጸዋል።
ሥራ አስኪያጁ የሀገር ውስጥ የዘይት ፋብሪካዎች የተሟላ የዘይት ማጣሪያ ያላቸው እንዲሆኑ ለማድረግ ስትራቴጂ ተቀርጾ ሥራዎች መጀመራቸውንም ተናግረዋል።
ለዘይት ምርት የሚሆኑ የጥሬ እቃ አቅርቦቶች ማለትም፤ የኑግ፣ የሰሊጥ፣ የሱፍ አበባ እንዲሁም ሌሎች የቅባት እህሎችን በሚፈለገው ልክ ለማምረት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ስለመደረጉም ጨምረው አስረድተዋል።
ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት የሀገር ውስጥ ምርት ካለው 3 በመቶውን ብቻ ይይዝ እንደነበር በማስታወስ፤ አሁን ላይ የምርት አቅርቦቱ ወደ 20 በመቶ መጠጋቱን አንስተዋል።
በተጨማሪም ዘይት ማጣሪያ ያላቸው ፋብሪካዎች በቁጥር አነስተኛ እንደነበሩ የገለጹ ሲሆን፤ ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሃብቶች ማነስ እና የገንዘብ ችግር ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱን አመላክተዋል።
በኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ በሥራ ላይ ያሉ እውቅና የተሰጣቸው ዘይትን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች 34 መሆናቸውን፤ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መግለጹ ይታወቃል።