ጥር 5/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ ጃባሊያ ውስጥ በግዳጅ የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያንን በተጠለሉበት ትምህርት ቤት ላይ በፈፀመችው የአየር ጥቃት 70 የሚደርሱ ሕጻናትን ገድላለች ሲል የጋዛ ሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ወንጅሏል።
ከእነዚህ 70 ሕጻናት በተጨማሪም በትንሹ 8 ሰዎች መገደላቸውን ኤጄንሲዉ ገልጿል።
በጋዛ ውስጥ ያሉ የፍልስጤማውያን ሕጻናት ከእስራኤል ወረራ ጋር በተያያዘ ከባድ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑ የተገለጸም ሲሆን፤ ጥቃቱ ከተጀመረ 16ተኛ ወሩን ይዟል፡፡
በሰሜን ጋዛ ለ100 ቀናት የቀጠለው የእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ 5 ሺሕ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ወይም ጠፍተዋል ሲሉ የሀገሪቱ የሕክምና ባለሙያዎች ለአልጀዚራ የገለጹ ሲሆን፤ በጥቃቶቹ ሌሎች 9 ሺሕ 500 የሚሆኑ ሰዎች መቁሰላቸውንም ተናግረዋል።
በአጠቃላይ እ.ኤ.አ. ከጥቅምት 7 ቀን 2023 ጀምሮ በጋዛ ሰርጥ እስራኤል እያሰነዘረችው ባለው ተደጋጋሚ ጥቃት፤ ቢያንስ 46 ሺሕ 565 ፍልስጤማውያን ሲገደሉ 109 ሺሕ 660 ቆስለዋል ሲል የፍልስጤም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የዚህ ጥቃት ሰለባዎች ደግሞ በአብዛኛው ሴቶች እና ሕጻናት መሆናቸውን አመላክቷል፡፡
ሚኒስቴሩ ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 28 ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ሲልም ገልጿል።
በሰሜናዊ ጋዛ ከሚገኘው የጃባሊያ የስደተኞች ካምፕ እስራኤል ፈጸመችው የተባለው የአየር ጥቃት አሰቃቂ መሆኑም የተገለጸ ሲሆን፤ 70 የሚደርሱ ሕጻናት ከመገደላቸው በተጨማሪ በርካታ ሰዎች በጥቃቱ መቁሰላቸውም ተነግሯል፡፡
ይህ ክስተት የተፈፀመው ደግሞ፤ "የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከሃማስ ጋር የተኩስ አቁም እና ምርኮኛ ልውውጥ ድርድር ለማድረግ፤ የሞሳድ የጸጥታ ኤጀንሲ ኃላፊዎችን ጨምሮ ከፍተኛ ተደራዳሪዎችን ወደ ኳታር ልከዋል" እየተባለ በሚነገርበት ወቅት መሆኑ ተገልጿል።
በሕዳር ወር 2024 የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትራቸው ዮአቭ ጋላንት በጋዛ በፈጸሙት የጦር ወንጀሎች የእስር ማዘዣ ማውጣቱ ይታወሳል።