ታሕሳስ 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የዩኒቨርሲቲ አመራሮች በአካባቢያዊና በመንደር የሚመድቡበት ሥርዓት መቆም አለበት በሚል በርካታ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ከጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት ጋር ውይይት ያካሄዱ ሲሆን፤ በዚህም ወቅት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ሚኒስቴሩ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራትን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለይም የዩኒቨርሲቲ አመራሮች በአካባቢያዊና በመንደር የሚመድቡበት ሥርዓት መቆም አለበት በሚል በርካታ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን አንስተዋል።
"ዩኒቨርሲቲዎች ዓለም አቀፍ የሆነ እውቀት የመማሪያና የማስተማሪያ ተቋማት እንጂ የአንድ አካባቢን ሰዎች ተቀብለው የሚያስተናግዱ አይደሉም" ያሉት ሚኒስትሩ፤ "ይህም ከዩኒቨርሲቲ መሰረታዊ ተልዕኮ ጋር የሚሄድ ባለመሆኑ መቀየር ይገባል በሚል፣ አዲስ የሚመደቡና የሚቀየሩ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች እንደ መርህ በችሎታና በውድድር ብቻ የመመደብ ሥራ እየተሰራ ይገኛል" ብለዋል።
በዚህም የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲን ካለበት መሰረታዊ ችግር ለማላቀቅ የአመራር ለውጥ ከተደረገ በኋላ ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑንም አብራርተዋል።
አክለውም ዩኒቨርሲቲዎች እውቀትና እውነት የሚገበይባቸው ትክክለኛ የማስተማሪያና የምርምር ተቋማት ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ፕሮፌሰር ብርሃኑ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብም በቁጭትና በእልህ ዩኒቨርሲቲውን ካለበት ችግር በማውጣት ጥሩ ትምህርት የሚሰጥበትና ለአካባቢው ማህበረሰብ ብሎም፤ ለሀገር የሚጠቅሙ ምርምሮች የሚሰሩበት ተወዳዳሪ ተቋም እንዲሆን ሊሰሩ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።