ታሕሳስ 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የእንስሳት መኖ እጥረት ለመፍታት ቢያንስ፤ በእያንዳንዱ ክልል ማቀነባበርያ ፋብሪካዎች እንዲከፈቱ ስትራቴጂ ነድፎ እየሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ከዚህ ቀደም በትግራይና ሲዳማ ክልሎች የማስጀመር ስምምነቶች የተደረጉ ሲሆን፤ አሁን ላይ ወደ ሌሎች ክልሎች በማስፋት የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪኮች እንደሚከፈቱ የሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ አበባ ታመነ ለአሐዱ ተናግረዋል።

የእንሰሳት መኖ አቅርቦት ችግር በዘርፍ ልማት ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ መፍጠሩ የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ በሚፈለገው ልክ ለመንቀሳቀስ እንዳይቻል ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት በአገር ውስጥ የእንስሳት መኖ አቀናባሪ ፋብሪኮችን መገንባት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙ ሲሆን፤ "ለዚህም በግብርና ሚኒስቴር በኩል ፍላጎት መሰረት ያደረገ ምርት እንዲመረት ይደረጋል" ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽንን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሬን ለማዳን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን ሰፊ ሥራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተፈላጊ የሆነው የዶሮ መኖ መሆኑን የሚታወቅ ሲሆን፤ ሁሉንም አይነት አካታች የእንስሳት መኖ በአገር ውሰጥ ለማምረት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ከሰሞኑ በአዲስ አበባ አንድ ፋብሪካ ለመክፈት በእቅድ መያዙንም የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሯ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡