ታሕሳስ 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጃዊ ወረዳ የሚገኘው የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች፤ በፋብሪካው እስካሁን እያገለገልን ቢሆንም፤ ለ4 ወራት ያህል ወርሀዊ ደመወዛችን ስላልተከፈለን በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንገኛለን ሲሉ ለአሐዱ አቤቱታቸውን አቅርበዋል።

ከሠራተኞቹ መካከል የአራት እና የ5 ቤተሰብ አስተዳዳሪዎች መኖራቸው የገለጹት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ "አሁን ላይ ደመወዝ በወቅቱና በተገቢው ሁኔታ ባለመሰጠቱ ምክንያት ቤተሰቦቻቸው ጭምር ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል" ብለዋል።

አክለውም "ደመወዝ በወቅቱ ባለመከፈሉ በቀን አንዴ እንኳን መመገብ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል" ያሉ ሲሆን፤ ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት ደመወዛቸው በአፋጣኝ ሊከፈል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ሠራተኞቹ የፋብሪካው አስተዳደር እንዲሁም የክልል እና የፌደራል መንግሥት አካላት የችግሩን አሳሳቢነት ግምት ውስጥ በማስገባት በአስቸኳይ መፍትሄ ይስጡን ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

አሐዱም የሠራተኞቹን ቅሬታ በመያዝ "ደመወዝ ያለመከፈሉ ምክንያት ምንድን ነው?" ሲል የሀገር አቀፍ እርሻ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ገበየሁ አዱኛን ጠይቋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በሰጡት በምላሽም ጉዳዩ ልክ መሆኑን ገልጸው፤ "ሰዎች የከፋ ችግር ላይ መሆናቸውን ተመልክተናል። ችግሩ እንዲፈታ ከኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጋር በመሆን ተነጋግረናል" ብለዋል።

አክለውም፤ "ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልነው እንገኛለን" ያሉ ሲሆን፤ የሠራተኞቹን የደመወዝ ክፍያ በሚመለከት ከኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ጋር በመሆን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለሚመራውን ከኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ቦርድ ጥያቄውን አስገብተናል ብለዋል፡፡

"በቀጣይም ከበላይ አካላት ምላሽ እስከምናገኝ ሠራተኞቹ በትዕግስት ይጠብቁ" ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

በስኳር ፋብሪካው ከ1 ሺሕ 500 በላይ ሠራተኞች መኖራቸውንና ሁሉም ሠራተኞች ለ4 ወራት ያህል ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው፤ እንዲሁም ለከፋ ችግር መጋለጣቸው ከተቋሙ ሠራተኞች ለማወቅ ተችሏል፡፡

የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 495/2014 ዓ.ም በቦርድ እንዲመራ ተወስኖ በ2015 ዓ.ም ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ምርት ማምረት የሚችልበት ደረጃ ላይ መድረሱ መገለጹ ይታወሳል፡፡

ነገር ግን ለሥራ ማስኬጃ በቂ በጀት ባለመመደቡ፣ የቁንዝላ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ትራንስፎርመር ብልሽት ከሁለት ዓመት በላይ አለመጠገን እና ሌሎች ወቅታዊ ሁኔታዎች ሳይፈቱ በመቅረታቸው ምክንያት በ2016 ዓ.ም ስኳር ማምረት አለመቻሉን ገልጿል፡፡

በዚህ ምክንያት በተፈጠረው የገንዘብ እጥረት ፋብሪካው ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል ስላልቻለ ከ15,655 በላይ ሠራተኛ እና የሠራተኛ ቤተሰብ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባቱን አስታውቋል፡፡