ጥር 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የሚመራውን የጫካ ፕሮጀክት እየገነባ የሚገኘው ኦቪድ ሪልስቴት፤ የዘመናዊ ከተማ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩን በትናንትናው ዕለት በይፋ አካሂዷል፡፡
በግንባታ ማስጀመሪያ እና በሽያጭ ቢሮ ማስተዋወቂያ መርሃ-ግብሩ ላይ እንደተባለው፤ በ20 ቢልዮን ብር በጀት በ5 ዓመታት ውስጥ የሚገነቡት መኖሪያ ቤቶች የመሬት መንቀጥቀጥን የሚቋቋሙ ቅንጡ አፓርትመንቶች ናቸው፡፡
የመኖሪያ መንደር ግንባታው የካ አባዶን፣ ጣፎ ከሚሽንን እና ሲኤምሲን የሚያገናኝ የመንገድ እንደሚኖረው ተነግሯል፡፡
የሚገነቡት መኖሪያ ቤቶች ከ60 ካሬ ጀምሮ ከአንድ እስከ ሦስት መኝታ ቤት ይኖራቸዋል የተባለ ሲሆን፤ በአጠቃላይ 9 ነጥብ 46 ሄክታር ላይ የሚያርፍ የመኖሪያ መንደር መሆኑም ተገልጿል።
ቅንጡ የመኖሪያ አፓርትመንቶችን፣ የገበያ ማዕከል፣ የሕጻናት ማቆያ፣ የጂምናዝየም፣ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤትን ጨምር በርካታ አገልግሎት የሚሠጡ ተቋማት ያካተተ መሆኑም ተነግሯል።
የመኖሪያ መንደሩ በዋጋው ላይ እስከ ጥምቀት በዓል የሚቆይ ልዩ የበዓል ቅናሽ አድርጓል የተባለ ሲሆን፤ በቅድሚያ ለሚገዙ የተሻለ እድል እንደሚኖርም ተመላክቷል፡፡