ጥር 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ትናንት ምሽት በደቡባዊ ኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የታየው ክስተት የሰው ሰራሽ ጠፈር ስብርባሪ ወደ ምድር ንፍቀ ክበብ ሲመለስ የተፈጠረ መሆኑን የአውሮፓ ስፔስ ኤጀንሲ ገልጿል።
በትናንትናው ዕለት ከምሽቱ 1:30 ገደማ በኢትዮጵያ በተለይም በደቡብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍሎች "ከዚህ በፊት ያልተለመደ ተቀጣጣይ እሳት መሰል ነገር በሰማይ ላይ መታየቱን" የአካባቢዎ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በዚህ ዙርያ የአውሮፓ ስፔስ ኤጀንሲ (European Space Agency) ለመሠረት ሚድያ በሰጠው ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ የታየው ክስተት ሰው ሰራሽ የጠፈር ቁስ ስብርባሪ ወደ ምድር ንፍቀ ክበብ ሲመለስ (re-entry) ሲያደርግ መሆኑን ገልጿል።
ኤጀንሲው አክሎም ስብርባሪው የቻይናው ሺጂያን-19 (ShiJian-19) ሊሆን እንደሚችል ጨምሮ ገልጿል።
"በየዓመቱ ከመቶ ቶን በላይ የሰው ሰራሽ የጠፈር ቁሶች ከቁጥጥር ውጭ ሆነው ወደ መሬት ይመለሳሉ" ያለው የአውሮፓ ስፔስ ኤጀንሲ፤ "ይህም በየዓመቱ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ክስተቶች መታየት ምክንያት ነው" ብሏል።
አክሎም "አንዳንዱ [የጠፈር ቁስ ስብርባሪ] መሬት ላይ ሊወድቅ ይችላል፣ ነገር ግን እንደ ጠፈር ሮኬት ያሉ ሁሉንም ቁሶች ተቆጣጥሮ ሰው በማይኖርበት አካባቢ እንዲወድቁ ማድረግ አይቻልም። አነስተኛ ቁሶች ራሳቸው ተቃጥለው ያልቃሉ፣ ትልልቅ አካላትን ግን ተቆጣጥሮ ወደ ምድር መመለስ ገና እያደገ ያለ ቴክኖሎጂ ነው። እድገቱም ዘገምተኛ ነው" በማለት የኤጀንሲው ቃል አቀባይ ለሚድያው ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦፓሻል ኢኒስቲትዩት በትናንትናው ምሽት በደቡብ ኢትዮጵያ ክፍል ሰማይ ላይ እየተቃጠለ ተቆራርጦ ወደ ምድር ሲጓዝ የታየው ቁስ በሰው ሰራሽ የስፔስ ቁስ ምክንያት የተከሰተ ሊሆን እንደሚችል ገልጿል፡፡
በኢኒስቲትዩቱ የከባቢ አየር ሳይንስ ተመራማሪ የሆኑት ገመቹ ፋንታ (ዶ/ር) ከኢቢሲ ዶት ስትሪም ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ "ጊዜ ያበቃላቸው ሳተላይት እንዲሁም ሳተላይቶችን የመጠቁባቸው የሮኬት ቁርጥራጮች ሊሆኑ ይችላሉ" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በማንኛውም ሰው ሰራሽ መንገድ ህዋ ላይ የሚንቀሳቀሱ ነገሮች ሊኖሩ ስለሚችሉ ወደ ከባቢ አየር ውስጥ ሲገቡ የመቃጠል እና ተሰባብሮ የመውረድ ምልክቶችን እንደሚያሳዩ የገለጹም ሲሆን፤ ክስተቱ የተፈጠረው በተፈጥሮአዊ የህዋ አካላት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
ከመሬት እና ከሶላር ሲስተም አፈጣጠር አንጻር አለቶች በመኖራቸው በማንኛውም ጊዜ እየተቆራረጡ ሊወርዱ እንደሚችሉም አመላክተዋል፡፡
በዓለም ላይ እንደዚህ ያለ ሁነት እንደሚከሰቱ የሚናገሩት ተመራማሪው፤ አልፎ አልፎ ቁጥራቸው በርከት ያሉት ወደ ምድር እንደሚወርዱም ገልጸዋል፡፡
ሰው የሚኖርበት ቦታ ከ4 እስከ 5 በመቶ እንደማይበልጥ የተናገሩት ተመራማሪው፤ ተቆራርጠው የሚወርዱ ነገሮች ከሰው ዕይታ ውጪ የሚከሰቱበት ሁኔታው ስለመኖሩም ጠቅሰዋል። አልፎ አልፎ ግን ለሰው ዕይታ እንደሚጋለጡም አስረድተዋል፡፡
ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዓመት እስከ 6 ሺሕ ድረስ ተቆራርጠው ምድር የሚደርሱ እና አለፍ ሲልም የአሸዋ ቅንጣት በመሆን ወደ ምድር የሚወርዱ ስለመኖራቸው ነው ተመራማሪው የተናገሩት፡፡
የሚቃጠሉበት ምክንያት ደግሞ ወደ ከባቢ አየር ሲገቡ ከከባቢ አየር ጋር በሚያደርጉት ፍትጊያ የሚፈጠር ስለመሆኑም አያይዘዋል፡፡
"አሁን እንዳለን መረጃ በደቡባዊ ክፍል የታየው ምስል ሰማይ ላይ እየተቃጠለ ነው የሄደው፤ አርፏል አላረፈም የሚለውን እስካሁን ማወቅ አልቻልንም" ብለዋል፡፡
የጠፈር ስብርባሪ ማለት አገልግሎታቸው ያበቃ ሳተላይቶች፣ ግልጋሎት የማይሰጡ መንኩራኩሮች፣ የሮኬት ማቀጣጠያ ተተኳሾች፣ ከጠፈር ላይ ግጭት የተረፉ ስብርባሪዎች እንዲሁም፤ በጠፈር በረራ ወቅት ተገንጥለው ያመለጡ ቁሳቁሶች ሊሆኑ እንደሚችሉ መረጃዎች ይጠቀማሉ።
እነዚህ በከፍተኛ ፍጥነት የሚጓዙ ስብርባሪዎች ለሌሎች ሳተላይቶች ስጋት ቢሆኑም፤ መሬት ላይ ላሉ ሰዎች የሚፈጥሩት የሞት ወይም የአካል ጉዳት ስጋት ከአንድ ትሪሊየን ውስጥ አንድ ብቻ መሆኑን የ 'ዘ ኦሮስፔስ ኮርፖሬሽን' መረጃ ይጠቁማል።
በትናንትናው ዕለት በደቡብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የታየው ክስተት በኬንያ ሰሜናዊ ምስራቅ ክፍል በቱርካና፣ ማርሳቢት፣ ሞያሌ አካባቢም መታየቱ ተገልጿል።
በደቡባዊ ኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የታየው ክስተት የሰው ሰራሽ ጠፈር ስብርባሪ ወደ ምድር ንፍቀ ክበብ ሲመለስ የተፈጠረ መሆኑን የአውሮፓ ስፔስ ኤጀንሲ ገለጸ
"ክስተቱ በሰው ሰራሽ የስፔስ ቁስ ምክንያት የተከሰተ ሊሆን ይችላል" የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦፓሻል ኢኒስቲትዩት
