ጥር 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የሻይ ቅጠል ምርትን ወደ ውጭ ለመላክ ፈቃድ ከተሰጣቸው ሦስት ተቋማት መካከል ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ላይ የሚገኘው አንድ ተቋም ብቻ መሆኑን የቡና እና ሻይ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
ባለስልጣኑ የቡና የወጪ ንግድ ላይ አበረታች ነገሮች እየታዩ ቢሆንም፤ በሻይ ቅጠል ምርት ላይ ያለው የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ደካማ የሚባል ስለመሆኑ አንስቷል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር ሻፊ ኡመር፤ በአሁኑ ወቅት ፈቃድ ከተሰጣቸው ሦስት ተቋማት መካከል ምርቶችን ወደ ውጭ የሚልከው አንድ ተቋም ስለመሆኑ የገለጹ ሲሆን፤ "ቀሪዎቹ የሀገር ውስጥ የሻይ ቅጠል ፍላጎት በመጨመሩ የተነሳ የሀገር ውስጥ ሽያጭ ላይ ብቻ ትኩረት አድርገዋል" ብለዋል።
በኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት የሻይ ምርትን የሚያመርቱት ኢትዮ አግሪሴፍት፣ ኢስት አፍሪካና ቨርዳንታ ድርጅቶች ብቻ መሆናቸውን የገለጹት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ እስካሁን ወደ ውጭ የሚልከው ኢትዮ አግሪሴፍት ብቻ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ዘርፉ የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ስላለው ባለስልጣኑ ተቋማቱን ጠርቶ ምርታቸውን እንዲያሳድጉና፤ በተሰጣቸው ፍቃድ መሰረት ወደ ውጪ የመላክ ሥራን እንዲሰሩ የመጨረሻ ማስንቀቂያ እንደተሰጣቸው ነግረውናል።
"የሀገር ውስጥ የሻይ ቅጠል ፍላጎት እየጨመረ በመሄዱ ምክንያት ወደ ውጪ የሚላከው የሻይ ቅጠል ምርት እጥረት እንዳይከሰት ለማድረግም፤ ምርቱን ከማስፋት አንጻር በርካታ ሥራዎች መሰራት እንዳለባቸው አቅጣጫ ተቀምጧል" ያሉት አቶ ሻፊ፤ በዚህም መሰረት ሰፊ ማሳዎች በሻይ ምርት እየተሸፈኑ እንደሚገኙ አክለዋል፡፡
በዚህም በኦሮሚያ ክልል በጅማ፣ በቡኖ በደሌ፣ በኢሉባቡር ዞኖች 7 ሺሕ የሚጠጋ ሄክታር የሚሸፍን ሻይ ቅጠል በምርት ሂደት ላይ እንደሚገኝ ያስታወሱ ሲሆን፤ ከማምረት ባሻገር የማቀነባበሪያ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነም ነግረውናል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ