ጥር 14/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት፤ ማኅበረሰቡ የተቋሙ መለያ የታተመባቸውን መድኃኒቶች እንዲጠቀም ማሳሰቢያ አስተላልፏል፡፡
ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጠ፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ እንዲሁም ከበድ ያለ የጎንዮሽ ጉዳት የሚያስከትለኩ መድኃኒቶች በገበያው መሰራጨታቸውን ተከትሎ፤ ተገልጋዩ መድኃኒቶችን ከመውሰዱ በፊት ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አወል ሀሰን፤ "ሕብረተሰቡ ከመድኃኒት መደብሮች የሚገዛቸውን መድኃኒቶች ከመውሰዱ በፊት የመድኃኒቶቹን ሕጋዊነት እና በኢትዮጵያ እንዲሸጡ ፈቃድ ማግኘታቸውን ማረጋገጥ አለበት" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በሀገር ውስጥ የሚመረቱትም ሆነ ከውጭ ሀገር የሚገቡት እንዲሁም በእርዳታ ወደሀገር ውስጥ የሚገቡት መድኃኒቶች የጥራት ፍተሻ ተደርጎላቸው ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲቀርቡ ሲፈቀድ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት መለያ እንደሚታተምባቸው የገለጹም ሲሆን፤ ማኅበረሰቡም መለያ የታተመባቸውን መድኃኒቶች በመመልከት ፈቃድ ያገኙትን በቀላሉ መለየት እንደሚችል አብራርተዋል፡፡
አሰራሩ ተቆጣጣሪ አካላት የመድኃኒቱን ሕጋዊነት በቀላሉ መቆጣጠር የሚያስችላቸው ስለመሆኑም ያነሱት አቶ አወል፤ ወደፊት ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምርቶቹን ማንኛውም አካል በቀላሉ እንዲለያቸው የሚያደር አሰራር ለመተግበር በሂደት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ