ጥር 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በዛሬው ዕለት ጥር 1 ቀን 2017 ዓ.ም 6ኛው ዙር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ጉባዔ ተካሂዷል፡፡
በጉባኤውም የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ በሕግና ፍትህና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት ቀርቦ የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ በ4 ድምፀ ተዓቅቦ እና 3 ተቃውሞ በአብላጭ ድምፅ ረቂቅ አዋጁ ጸድቋል፡፡
የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግስቱ ረቂቁ ወደ ኮሚቴው ከቀረበ ጊዜ ጀምሮ ካስረጂዎች ጋር እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተደጋጋሚ ውይይት እንደተደረገበት ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡
በዛሬው ዕለት የፀደቀው አዋጅ 'ከውጪ የተላከ ገንዘብ ነው' የሚል ማንኛውም ግለሰብ ገንዘቡ በሕጋዊ መንገድ በባንክ ሥርዓት ውስጥ ያለፉ ግብይቶች ወይም ክፍያዎች ስለመሆናቸው በተገቢው የባንክ ደረሰኝ አስደግፎ ማቅረብ የሚገባ ሲሆን፤ ከዚህ ውጪ ያለው ግን እንደ 'ምንጩ ያልታወቀ ገቢ' ተደርጎ ይቆጠራል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ክስ የሚቀርብበት ጊዜ እና የገንዘብ መጠን ተደንግጓል፡፡
በዚህም አዋጁ ወደኋላ 10 ዓመታት ተመልሶ የሚሠራ ሲሆን፤ ይህንንም ለመክሰስ የ10 ሚሊዮን የገንዘብ ገደብ ተቀምጧል፡፡
ማንኛውም ሰው በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ ያለው ንብረት ወይም የኑሮ ደረጃው አሁን ላይ ባለበት ወይም አስቀድሞ በነበረበት ሥራ ወይም በሌላ መንገድ ከሚያገኘው ሕጋዊ ገቢ የማይመጣጠን እንደሆነ ካላስረዳ በስተቀር ንብረቱን ይወረሳል ይላል፡፡
ሌላው የንብረቱን ወይም የኑሮ ደረጃውን ምንጭ በተመለከተ ምክንያታዊ የሆነ የወንጀል ጥርጣሬ በኖረ ጊዜ፤ የዚህ አይነቱ የኑሮ ደረጃ ወይም ያለው ንብረት እንዴት ሊኖረው እንደቻለ ለፍርድ ቤት ማስረዳት እንዳለበትም ረቂቁ ይገልጻል፡፡
በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ያፈራው ንብረት ማለት በራሱ ስም የሚገኝ ንብረት፣ በራሱ ስም ባይሆንም ለራሱ ጥቅም ሲያዝበት ወይም ሲቆጣጠረው የነበረው ንብረት፣ የተጠቀመው ወይም ደግሞ ያስወገደው ንብረት፣ በሽያጭ፣ በስጦታ ወይም በማንኛውም ሁኔታ ያስተላለፈውን ንብረት ይጨምራል፡፡