ጥር 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ዞን በ3 ወረዳዎች ብቻ፤ 6 ሺሕ 300 የሚሆኑ እንሰሳቶች መሞታቸውን የዞኑ አደጋ ስጋት እና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ለአሐዱ በላከዉ መረጃ አስታውቋል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት ማለትም ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ በተደረገው ጥናት መሰረት የክረምት ዝናብ ባለመዝነቡ ምክንያት የሞቱ እንሰሳት የዳልጋ ከብት 750፣ ጋማ ከብት 135 እና በግና ፍየፈል 5 ሺሕ 415 አጠቃላይ ወደ 6 ሺሕ 300 እንሰሳት መሞታቸውን አስታዉቋል።

621 ሰዎች ለችግር እና ለድርቅ መጋለጣቸውንም ዞኑ ለአሐዱ በላከው መረጃ ገልጿል፡፡

በተለይ ሰሀላ፣ ዝቋላ እና አበርገሌ በ3ቱም ወረዳዎች ለተከታታይ ዓመት የክረምት ዝናብ ባለመኖሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ለከፋ ችግር እየተጋለጡ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከአካባቢያቸዉ ለቀዉ ወደ አጎራባች ቦታዎች እንሰሳቶች እየተሰደዱ መሆኑን አመላክቷል።

በአጠቃላይ 104 ሺሕ 796 እንሰሳቶች ወደ ምስራቅ በለሳ፣ ሰሜን በር፣ ጃን አሞራ እና መሰል አጎራባች ቦታዎች መሰደዳቸውም ተገልጻል፡፡