መጋቢት 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) አቢሲኒያ ባንክ ለሴት ሥራ ፈጣሪዎች የተዘጋጀና ከመጋቢት 16 እስከ መጋቢት 18 ቀን 2017 ድረስ የሚቆይ የንግድ አውደ ርዕይ በመስቀል አደባባይ ማዘጋጀቱን አስታውቋል።

የንግድ አውደ ርዕዩ ማርች 8 በማስመልከት "እችላለው " በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የነበረው የደም ልገሳ፣ አደይ እና ዛህራን መርሃ ግብር ማስተዋወቅ እና የሙዚቃ ውድድር አንድ አካል መሆኑ ተገልጿል።

ዝግጅቱ በሴቶች የሚመሩ የንግድ ድርጅቶችን ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያሳዩበት መድረክ በማዘጋጀት፣ ትስስራቸውን ለማስፋት እና አዳዲስ የገበያ ዕድሎችን ለማግኘት ያለመ ነውም ተብሏል።

Post image

የንግድ አውደ ርዕዩ ከ100 በላይ በሴቶች የሚመሩ የተለያዩ የንግድ ሥራዎችን ያካተተ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል እንደ ፋሽን፣ ግብርና፣ የውበት መጠበቂያ እና የእጅ ሥራዎች ያሉ ዘርፎችን ማካተቱ ተነግሯል።

በዕለቱ ተጋባዠ የነበሩት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሴቶችን የማብቃት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ትሁኔ ስንሻው፤ ባንኩ ሴቶችን በገንዘብ በማካተት እና በኢኮኖሚ ድጋፍ ለማድረግ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።

የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን እና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን በማጎልበት ረገድ የሚጫወቱትን ሚና በማሳየት፤ መሰል ተነሳሽነቶችን ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌሎች ተቋማትም ሴቶችን ማዕከል ባደረጉ መርሃ ግብሮች ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በማሳሰብ፤ ማህበረሰቡን በማጠናከር እና ሀገራዊ እድገትን በማጎልበት ላይ ያላቸውን አስተዋፅዖ በመገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

ባንኩ በሴቶች የሚመሩ የንግድ ሥራዎችን ለመደገፍ እና የሴቶችን የኢኮኖሚ ተሳትፎ ለማበረታታት ከዚህ በፊት ከዋስትና ነፃ እና በዝቅተኛ ወለድ የቀረበ ለሴት ሥራ ፈጣሪዎች 55 ሚሊዮን ብድር መስጠቱን አስታውሰዋል።

ባንኩ የሴት ሥራ ፈጣሪዎችን ለማብቃት የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ እና የንግድ እድገትን በማመቻቸት ያለውን ቁርጠኝነት አፅንዖት ሰጥተዋል።

"ይህ ተነሳሽነት እንደ ሀገር ሥርዓተ-ፆታን ያካተተ የኢኮኖሚ ልማትን ለማስፋፋት የሚደረገው ሰፊ ጥረት አጋዥ ነው" ብለዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ