የካቲት 5/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) 46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ዛሬ በሕብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡

ስብሰባው "የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን" በሚል መሪ ሀሳብ ነው የሚካሄደው።

በሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባው የአፍሪካ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶችና የሕብረቱ ተቋማት አመራሮች እንደሚሳተፉ ሕብረቱ አስታውቋል።

በዚህም ምክር ቤቱ ባለፈው ወር የአፍሪካ ሕብረት ቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ በተወያየባቸው አጀንዳዎች ላይ ምክክር እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡

Post image

በተጨማሪም በሕብረቱ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ምክር ቤቱ በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሥር የሚገኙ የስድስት ኮሚሽነሮችን ምርጫ ያካሄዳል።

እንዲሁም የአፍሪካ የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት የአምስት አባላት ምርጫ እንደሚካሄድ ከሕብረቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከ2025 እስከ 2027 ድረስ ለሦስት ዓመታት ለሚቆየው የምክር ቤት የአባልነት እንደምትወዳደርም ተገልጿል።

የካቲት 8 እና 9 ቀን 2017 ዓ.ም ደግሞ፤ 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ አዲስ አበባ ይካሄዳል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ