የካቲት 5/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአፋር ክልል ሃላይደጌ-አሰቦት ፓርክ ባለፈው ቅዳሜ ተከስቶ የነበረው የእሳት ቃጠሎ ከሦስት ቀናት ርብርብ በሗላ፤ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል።

የእሳት ቃጠሎውን ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ የዱር እንሰሳት ጥበቃ ባለስልጣን መ/ቤት፣ የሃላይደጌ እና የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ሠራተኞች፣ የገቢ ራሱ ዞን እና አሚባራ ወረዳ ነዋሪዎችና አመራሮች እንዲሁም የሃላይደጌና አንዲዶ ቀበሌ ነዋሪዎች ርብርብ ማድረጋቸው ተገልጿል።

Post image

የእሳት ቃጠሎውን ለመቆጣጠር በሎደር የታገዘ እሳት የማጥፋት እና የቆረጣ ሥራ መሠራቱም ተገልጿል።

ለእሳቱ መባባስ ደረቅ የአየር ንብረት እና በአካባቢው ያለው ከፍተኛ ንፋስና ደረቅ ሣር ምክንያት እንደነበር ተመላክቷል።

የሃላይዳጌ አሰቦት ብሔራዊ ፓርክ ከ1965 ዓ.ም ጀምሮ የዱር እንስሳት ጥብቅ ቦታ ሆኖ የቆየው ሲሆን፤ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ብሔራዊ ፓርክ ደረጃ ያደገ ብሔራዊ ፓርክ ነው።

1099 ስኩዌር ኪሎ ሜትር አካባቢ ስፋት ያለው ብሔራዊ ፓርኩ፤ የ325 የእጽዋት ዝርያ፣ የ244 የአእዋፍ ዝርያ እና ከ42 በላይ አጥቢ እንስሳት መኖሪያ ፓርክ ስለመሆኑም ተመላክቷል።

Post image

በፓርኩ ላይ ባለፈው ቅዳሜ ከሰዓት አካባቢ ከፍተኛ መጠን ያለው እሳት ቃጠሎ ተከስቶ የነበረ ሲሆን፤ እሳቱን ለማጥፋት በተደረገው ርብርብ ትናንት ከሰዓት ጀምሮ በፓርኩ ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ