ጥር 5/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ የካ ክ/ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ማራቶን ሕንጻ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፤ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመግዛት እና በመሸጥ ሀሰተኛ የገንዘብ ኖት ወደ ማህበረሰቡ ሲያሰራጩ የነበሩ 7 ግለሰቦች ከነኤግዚቢቱ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራው መቀጠሉን የየካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።

ፖሊስ በቦታው ቁጥጥር በሚያደርግበት ሰዓት በገበያ ቦታዎች ሁለት ግለሰቦች አትክልት እና ፍራፍሬ ግብይት ሲያደርጉ በመጠራጠር ባደረገው ፍተሻ 14 ሺሕ 600 ሀሰተኛ ብር እንደተገኘባቸው ተገልጿል።

በዚህም መነሻነት ባደረገው ምርመራ የማስፋት ሥራ እና በሌላ አንድ ተጠርጣሪ ላይ በተደረገ አካላዊ ፍተሻ 18 ሺሕ 600 ሀሰተኛ ብር መያዙንም ፖሊስ መምሪያው አስታውቋል።

Post image

የወንጀሉን ምንጭ ለማወቅም ፖሊስ ምርመራ የማስፋት ተግባራትን ማከናወኑም የተገለጸ ሲሆን፤ የፍ/ቤት የመበርበሪያ እና የመያዣ ትዕዛዝ በማውጣት በዋና ዋና ተጠርጣሪዎች ላይ ባደረገው ብርበራ በአጠቃላይ 50 ሺሕ 200 ሀሰተኛ ብር እና 7 ተጠርጣሪዎችን ይዞ ምርመራ የማስፋት ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ ፖሊስ ገልጿል።

Post image

በተጨማሪም የተያዘውን ኤግዚቢት ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሾላ ቅርንጫፍ በመውሰድ ሀሰተኛ መሆኑን የማረጋገጥ ሥራ እንደተሰራ እና እንዲወገድ መደረጉንም ፖሊስ መምሪያው አመላክቷል።

ወደ ፊትም ሕገ ወጥ ተግባራትን እና መሰል ወንጀሎችን የመከላከሉን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቀሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ፤ ማህበረሰቡ እንደዚህ ዓይነት አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት ጥቆማ በመስጠት እና ትብብር የማድረግ የተለመደ ተግባሩን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ መልዕክቱን አስተላልፏል።