ጥር 5/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የሚገኙ ሀገር በቀል ምርቶችን፣ አገልግሎቶችን እና ፈጠራዎችን ለሁሉም እውቅና መስጠት የሚከብድ ቢሆንም፤ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ሊሸጡ እና የንግድ ትስስሩ ላይ ሊዘዋወሩ የሚችሉ ምርቶችን ደረጃ የማውጣት ሥራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ለአሐዱ ገልጿል።
"አሁን ላይ የሰዎች አኗኗር ዘይቤ እየተቀየረ ሲሄድ ምርቶችን በደረጃቸው መርጦ የመጠቀም ልምድ እየጨመረ ነው" የተባለ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ምርቶች በደረጃ ልክ ሲዘጋጁ ሁሉም እንደ ምርጫው ገዝቶ እንዲጠቀም እድል የሚሰጥ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት በቀለ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ያሉ ምርቶችን ሁሉ ደረጃ ማውጣት ባይቻልም ነገር ግን ከአፍሪካ ደረጃ አውጭ ድርጅት በጤፍ እና በእንጀራ የወጡ ደረጃዎች ላይ ስምምነት ተደርጓል፡፡
"ይህ መሆኑ የንግድ እንቅስቃሴን የሚያሳድግና የምርቶችንም ተፈላጊነት የሚጨምር ነው" ሲሉ አክለዋል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት በሀገር ውስጥ ላሉ ምርቶች፣ አገልግሎቶች እና የፈጠራ ሥራዎች ደረጃን ሲያወጣ ላለፉት 50 ዓመታት የቆየ ተቋም እንደመሆኑ፤ እስካሁን የመዘገባቸው የደረጃዎች ብዛት 12 ሺሕ 161 መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በሰባት ዋና ዋና ዘርፎች ማለትም፤ በምግብ እና የግብርና ውጤቶች፣ በኤሌክትሮ ቴክኒካል፣ በጤና እንዲሁም በኮንስትራክሽን እና በሲቪል ምህንድስና እንዲሁም በሌሎችም ዘርፎች ያወጣቸው ደረጃች መኖራቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር መሰረት በቀለ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም አስገዳጅ የሆኑ ደረጃዎች መኖራቸውን የገለጹም ሲሆን፤ በየዓመቱ ከሚወጡት ደረጃዎች ተጨማሪ የሚያስፈልግ ከሆነ በሚል ዳሰሳ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
"ተቋሙ ከመዘገባቸው ደረጃዎች ውስጥ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ከምግብ እና ግብርና ምርቶች ጋር የተያያዙ ደረጃዎች ናቸው" ሲሉም ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ደረጃዎችን ሲሰጥ የቆይታ ጊዜን እንደሚመለከት የተገለጸ ሲሆን፤ ቀጣይነት የሌለው ምርት ላይ ደረጃ እንደማይወጣ ነው የተነገረው፡፡
በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የሽሮ ደረጃ ሊወጣ እንደሆነ ተገልጾ የነበረ ሲሆን፤ "አሁን ላይም ይህ ደረጃ ወጥቶ ሥራ ላይ ውሏል" ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ምክር ቤት ባካሄደው 40ኛ እና 41ኛ ጉባኤው 350 ደረጃዎችን ማጽደቁም የሚታወስ ነው፡፡