ጥር 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከሰሞኑ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያ ምርጫ፣ የፖለቲካ ፖርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጁ ቁጥር 1162/2011 ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ማሰቡን አስታውቋል።
ለዚህም ይረዳው ዘንድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እያደረገ የሚገኘው ቦርዱ፤ በተለያዩ የአዋጁ አንቀፆች ላይ ማሻሻያ ማድረጉን ገልጿል።
አሐዱም "ለመሆኑ እየተሻሻለ የሚገኘው ረቂቅ ሕግ፤ በተለይም ከጠቅላላ ጉባኤ ጋር በተያያዘ ከቦርዱ ጋር ውዝግብ ውስጥ የሚገኘውን ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)ን በተመለከተ ምን ዓይነት መፍትሄ ይገኝለት ይሆን?" ሲል የቦርዱን ዋና ሰብሳቢ ጠይቋል።
የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ በምላሻቸው፤ "ከጠቅላላ ጉባኤ ጋር በተገናኘ በረቂቁ ላይም ሆነ በልዩ ሁኔታ የሚመዘገቡ ፖርቲዎች የሚተዳደሩበት ደንብ በመኖሩ፤ ሕጉ እና ደንቡ በሚያዘው መሠረት በቦርዱ የሚወሰን ይሆናል" ብለዋል።
ምርጫ ቦርድ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ፖርቲው ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግ የተሰጠውን ጊዜ እንዲጠቀም አሳስቦ እንደነበር ይታወሳል።
ይህንንም በሚመለከት ህወሓት ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ፤ "የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርዱ ጉባኤ አካሂዱ የሚለውን ጨምሮ ሌሎች ትዕዛዞችን ከመስጠት ተቆጥቦ፤ የተፈጠሩ ልዩነቶች በፓለቲካዊ ውይይት ለመፍታት የተጀመረው ጥረት በማስቀጠሉ ላይ ሊያተኩር ይገባል" ሲል ኳንኗል።
የቦርዱ ደንብ ቁጥር 1162/2011 ማንኛውም ፖርቲ በየሦስት ዓመቱ ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ እንዳለበት የሚገልጽ ሲሆን፤ በማሻሻያው ላይም "ጠቅላላ ጉባኤ ሲያደርግ የመንግሥት አዳራሾችን በነፃ መጠቀም ይችላል" ሲል ይገልጻል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ