ጥር 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ከመስከረም እስከ ታሕሳስ ወር ደመወዝ ያልተከፈላቸው መምህራን፤ ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተዳምሮ የጉልበት ሥራ ለመስራት ተገደዋል ሲል የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ለአሐዱ አስታውቋል፡፡
በአካባቢዎቹ ያሉ መምህራን ለተማሪዎቻቸው ሲሉ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ተቋቁመው እየሰሩ መቆየታቸውን የገለጸው ማህበሩ፤ "አሁን ላይ ግን ያለው ሁኔታ ካቅማቸው በላይ እየሆነ ነው" ብሏል፡፡
"ለወራት ደመወዝ ያልተከፈሉ መምህራን ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለስ ባለመቻላቸው የጉልበት ሥራ የሚሰሩ አሉ" ያሉት፤ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አበበ ናቸው፡፡
"በዚህም ቀጣዩ የመምህራኑ እጣ ፋንታ ምን እንደሆነ አይታወቅም" ያሉት የማህበሩ ምክትል ፕሬዝደንት የትምህርት ሥራውንም ወደ ኋላ ጎትቶታል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ትምህርት ባልተጀመረባቸው አካባቢዎች ያሉ ተማሪዎች ትምህርት ወደሚሰጥባቸው ቦታዎች ሄደው ለመማር ሲሞክሩ በአንዳንድ አካላት ይከለከላሉ የተባለ ሲሆን ተማሪዎቹም ወደነኝህ አካባቢዎች ሲሄዱ በተፈጠረ የቦታ ጥበት፤ በአንድ ክፍል ውስጥ 90 የሚሆኑ ተማሪዎች እንዲቀመጡ አስገድዷል ነው የተባለው፡፡
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ያሉ መምህራንን የተመለከቱ ችግሮች በሁሉም አካባቢ አይነት እና መጠናቸውን እየቀያየሩ መቀጠላቸውም ነው የተገለጸው፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ