ጥር 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ እውቅና ለመስጠት ስለመስማማቷ መግለጿን ተከትሎ፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለአንድ ዓመት ያህል የዘለቀ የከረረ ውዝግብ ውስጥ ገብተው ቆይተዋል።
ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ እና ወታደራዊ አለመግባባቶችን ፈጥሮ የቆየ ሲሆን፤ አለመግባባቱን ለመፍታትም በቱርክ አደራዳሪነት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሙሀሙድ ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተገናኝተው የሁለትዮሽ ምክክር አድርገዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ አሐዱ ካነጋገራቸው ከዘርፉ ባለሙያዎች አንዱ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው ጥላሁን ሊበን፤ "የሁለቱ ሀገራት ስምምነት ላይ መድረስ በጎ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ ግን ምላሽ ማግኘት አለበት" ብለዋል።
"የኢትዮጵያ መንግሥት የደረሰውን ስምምነት ተከትሎ ከሶማሊላንድ ጋር የነበረውን ክፍተት በማረም በሕጋዊ መንገድ ወደብ የሚያገኝበትን አማራጭ መፈለግ አለበት" ሲሉም አክለዋል።
"የወደብ ጥያቄን ከፖለቲካ መለየት ያስፈልጋል" ያሉት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው፤ ወደብ ለሀገር ኢኮኖሚ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ይህንን ሃሳብ የሚጋሩት የቀድሞው ዲፕሎማት ዶ/ር ተሻለ ሰብሮ በበኩላቸው፤ "ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያደረገችው ስምምነት የጠንካራ ዲፕሎማሲ ማሳያ ነው" ያሉ ሲሆን፤ ወደብ ለማግኘት ሰላማዊ መንገዶችና አማራጮችን ማየት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ብቻም ሳይሆን የሌሎች ጎረቤት ሀገራትን ወደብ ለመጠቀም ዲፕሎማሲያው ግንኙነቷን በደንብ ማጠናከር እንዳለባትም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ በርካታ ተቃውሞዎች ስለሚገጥሙት "ወደኃላ ማለት አያስፈልግም" ያሉት የቀድሞው ዲፕሎማት ዶ/ር ተሻለ፤ "በበሳል አመራር፣ ፖለቲካ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥበብ መከተል አለባት" ብለዋል።
አሐዱ ያነጋገራቸው ምሁራን ኢትዮጵያ ወደብ እንደሚያስፈልጋት አጽንኦት በመስጠት፤ ወደብ ለማግኘት ያሏትን ሰላማዊ አማራጮች በሙሉ መጠቀም እንዳለባት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ ጥር ወር በኤደን ባህረ ሰላጤ 25 ኪሎሜትር የሚረዝም የባህር ጠረፍ ለ50 ዓመት በሊዝ እንድትይዝና በምትኩ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ የሚያስችል ስምምነት ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር መፈራረሟ ይታወሳል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ