ጥር 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ የሂጃብ አለባበስ ላይ የተደረገው ክልከላ በሕገ መንግሥት የተቀመጠውን መብት የሚጥስ በመሆኑ፤ የሚመለከተው አካል ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳስቧል፡፡

የጉባኤው ምክትል ጠቅላይ ጸሐፊ መሱድ አደም፤ ከዚህ በፊት በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ የሙስሊሞች ሂጃብ አለባበስ ጋር በተያያዘ ተማሪዎች 'ተከልክለናል' የሚሉ ቅሬታዎችን ሲያሰሙ እንደነበር ያስታወሱ ሲሆን፤ በዚህም የክልሉ መጅሊስ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄቸው እንዲፈታ በአደባባይ ያቀረቡ መሆኑን አንስተዋል፡፡

አክለውም ይህንን ጉዳይ በሚመለከት እንደ ኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለፌደራል መንግሥቱ ጉዳዮ በሕገ መንግሥቱ መሰረት መፍትሄ እንዲሰጠው በፅሁፍ የጠየቀ መሆኑንም ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

ጉባኤው ያሉ ችግሮች እንዲስተካከሉ ከክልሉ መጅሊስ ጋርም በጋራ በመሆን እየሰራ እንደሚገኝ እና በቅርቡም ችግሮቹ የሚስተካከሉበት ሁኔታ እንደሚኖር ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአንድነት፣ በእኩልነትና በአብሮነት የምትታወቅ መሆኗን ያነሱት ምክትል ፀሃፊው፤ "አሁን እየተስተዋለ ያለው ችግር ግን ሕገ-መንግሥቱንና ሐይማኖታዊ ስርአቱን የሚጥስ በመሆኑ ሊስተካከል ይገባል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሕዝቦቿ ተከባብረው የሚኖሩባት ሀገር እንደሆነች ገልጸው፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጉዳዩን በውይይት እንደሚፈታው መግለጹንም ጠቁመዋል፡፡

ጉዳዩ እልባት የማይሰጠው ከሆነ በክልሉ ከሚገኘው መጅሊስ ጋር በጋራ በመሆን በድጋሚ ጥያቄያቸውን እንደሚያቀርቡም አጽንኦት ሰተዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ