ጥር 17/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ረቂቅ አዋጅ በርካታ ዝርዝር ጉዳዮች የያዘ በመሆኑ የፓርቲዎች እንቅሰቀሴ ላይ መጠነ ሰፊ ለውጥን የሚያመጣ መሆኑን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡

የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ሃይሉ፤ በረቂቅ ደረጃ የቀረበውና በውይይት ላይ የሚገኘው አዋጁ ከዚህ በፊት ጉድለት ተብለው ይነሱ የነበሩ ጉዳዮች ይፈታል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡

በተለይም ከዚህ ቀደም በጉድለት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል የነበረው የቅሬታ አፈተታ ስርዓት ጋር በተያያዘ በተለይም በ1162/2011 አዋጅ ላይ ከምርጫ ጋር ተያይዞ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ የሚቋቋመው ከምርጫ ክልል ቅርጫፍ ፅህፈት ቤት የነበረ መሆኑን አንስተዋል፡፡

አሁን ላይ ግን በአንድ ምርጫ ክልል ሦስት ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች እንደሚቀመጡ የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ "እነዚህ ቅሬታ ሰሚዎች በቀጣይ በመራጮች ምዝገባ ጊዜ ቁጭ ብለው የሚከታሉ ይሆናሉ" ብለዋል።

በመሆኑም ይህ ሂደት በተግባር ወርዶ ሲታይ መፈፀም ያልተቻለ ጉዳይ መሆኑን በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የታየ መሆኑንም ዋና ሰብሳቢዋ ጨምረው ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያለፉት ስድስት ዓመታት የተጠቀመውንና ስድስተኛ ዙር ሀገራዊ ምርጫን የመራበትን አዋጅ የማሻሻል ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

ለዚህም እንዲረዳው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ የሚገኘው ቦርዱ፤ ይህ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ቀርቦ ሲፀድቅ ለፓርቲዎች የሚሰጠው ጠቀሜታ ስለመኖሩ አሐዱ የቦርዱን ዋና ሰብሳቢ ጠይቋል፡፡

ሜላተወር ሃይሉ ሲመልሱም በተለይም ፓርቲዎች ለምርጫ በሚደረግ ዝግጅት ላይ ከውህደት እና ግንባር መፍጠር ጋር ያለነበሩ ዝርዝር ጉዳዮች የሚዳስስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እያደረገ ባለው የግብዓት ማሰባሰብ ውይይት ላይ ከፖርቲዎች በርካታ ግብዓቶችን እያገኘ መሆኑን በማንሳት፤ ነገር ግን ከዚህ ቀደም ፓርቲዎቹ ሲያነሱ የነበሩት አብዛኛው ጉዳይ በረቂቁ መካተቱን ገልጸዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ