ጥር 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአንዳንድ ሥነ-ምግባር በጎደላቸው የጤና ባለሙያዎች ምክንያት ለካንሰር ሕሙማን ሕክምና የሚውሉ መድኃኒቶች ላልተገባ ጥቅም ይውላል ሲሉ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ለአሐዱ ገልጿል፡፡
የአገልግሎቱ የሕዝብ ግንኙነት እና የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አወል ሀሰን፤ "መድኃኒቶች ወደ ታካሚዎች እንዳይደርስ ችግር የሆነብን በሕክምና ተቋማት ውስጥ የሚደረገው ቁጥጥር አነስተኛ መሆን መድኃኒቱ በትክክል አገልግሎት ላይ እንዳይውል እንቅፋት በመፍጠሩ ነው" ብለዋል፡፡
በቀጣይ ችግሩን ለመቅረፍ እነዚህ መድኃኒቶች በግል ፋርማሲዎች እንዳይሸጥ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ በተጨማሪም የቁጥጥር ሥራዎችን በማጠናከር ለመስራት መታቀዱን አንስተዋል፡፡
"የሙያ ሥነ-ምግባር በማይሰማቸው አንዳንድ ባለሙያዎች መደኃኒቱ ወጥቶ ይሸጣል" ያሉም ሲሆን፤ "ይህንን ለመቆጣጠር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ መድኃኒቶች በቀላሉ እንዲለዩ የመድኃኒት አቅርቦት ምልክት ተለጥፎባቸው የሚቀርቡ ቢሆንም፤ ችግሩን መቅረፍ አለመቻሉን ነው የገለጹት፡፡
![Post image](/_image?href=https%3A%2F%2Fcdn.sanity.io%2Fimages%2Fbede4k7t%2Fproduction%2Ff96465482f6339acf2f3272d616bb86afe53596c-720x772.jpg&w=720&h=772&f=webp)
አሁን ላይ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት 54 አይነት የካንሰር መድኃኒቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳስገባ የገለጹም ሲሆን፤ የገቡት መድኃኒቶች በጤና ሚኒስትር 50 በመቶ ድጋፍ ተደርጎባቸው ወደ ሀገር የገቡ መሆናቸው ተገልጿል።
"የገባው የካንሰር መድኃኒት ስርጭቱ በጤና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ መድኃኒት አገልግሎት እና የጤና ተቋማት በጋራ በመሆን ያሰራጫሉ" ሲሉም ኃላፊው ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
"የቱንም ያህል አቅርቦት ቢኖር የቁጥጥር ሥራ እስካልተሰራ ድረስ እጥረት ይከሰታል" ያሉት ኃላፊው፤ በዚህም ምክንያት የኅብረተሰቡን ቅሬታ መመለስ አዳጋች መሆኑን ገልጸዋል፡፡