ጥር 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) እስራኤል እና ሃማስ በጋዛ ሰርጥ ለ15 ወራት ሲያካሂዱት የቆየውን አውዳሚ ጦርነት በማቆም፤ በመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና ላይ ሰላም ለማስፈን መስማማታቸው ተገልጿል።

ስምምነቱ በመጀመሪያው ዙር የ6 ሳምንታት ቅድመ ተኩስ ማቆምን የያዘ ሲሆን፤ ይህም "ጦርነቱን በዘላቂነት ለማቆም እንዲሁም አሜሪካውያን ታጋቾችን ወደ አገራቸው ለማምጣት የሚያስችል ድርድርን ይፈቅዳል" ሲሉ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስታውቀዋል።

Post image

የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ሦስት ደረጃዎች ያሉት ነውም ተብሏል። በዚህም የመጀመሪያው በጋዛ በሃማስ ታጣቂዎች የተያዙ ታጋቾችን እና በእስራኤል ውስጥ የሚገኙ የፍልስጤም እስረኞች እንዲለቀቁ የሚፈቅድ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህም መሠረት በመጀመሪያው ዙር ሃማስ 33 ታጋቾችን እንዲሁም እስራኤል 2 ሺሕ የሚጠጉ የፍልስጤም እስረኞችን ለመልቀቅ መስማማታቸው ተመላክቷል።

በተጨማሪም ሁለቱ ተፋላሚዎች በጋዛ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ቃል መግባታቸው የተነገረ ሲሆን፤ በዚህም "የጋዛ ሁለት ሚሊዮን ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ይደርጋል" ተብሏል።

እንዲሁም ስምምነቱ በ15 ወራት ጦርነት ወደ ወደወደሙ ግዛቶች የሚፈልገውን ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ እንዲሁም፤ ነዳጅ ወደ ጋዛ እንዲገባ የሚፈቅድ መሆኑን አደራዳሪዎች አስታውቀዋል።

Post image

በስምምነቱ መሰረትም የእስራኤል ጦር ከጋዛ በ700 ሜትር ያህል ይርቃል የተባለም ሲሆን፤ ስምምነቱ ከተጀመረ ከሰባት ቀናት በኋላ እስራኤል የራፋህን መሻገሪያ ከግብፅ ጋር እንደምትከፍት ተመላክቷል።

ዓለም አቀፍ የረድኤት ተቋማት ስምምነቱን በደስታ እንደሚቀበሉት በመግለጽ፤ በጋዛ ውስጥ ሥራቸውን እንደሚያሳድጉ ቃል ገብተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ፤ በጦርነት ምክንያት የሚደርሰውን ስቃይ ለማስታገስ “ፈጣን፣ ያልተደናቀፈ እና ያልተቋረጠ ሰብዓዊ አቅርቦት” እንዲደረግ ጠይቋል።

Post image

ባደን ስምምነቱን አስመልክቶ ትናንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ፤ የእርሳቸው አስተዳደር እና የትራምፕ ቡድን በጋዛ ስምምነት ላይ "እንደ አንድ ይናገሩ ነበር" ብለዋል።

"ይህ ስምምነት በእኔ አስተዳደር ተዘጋጅቶ ድርድር ተደርጎበታል። ነገር ግን ውሉ በአብዛኛው በሚቀጥለው አስተዳደር ይተገበራል" ሲሉም መናገራቸውን ኤፒ ዘግቧል።

በተጨማሪም ባይደን "ንግግሮች ከጊዚያዊ የተኩስ አቁም አልፈው፤ “የጦርነቱ ዘላቂ ፍጻሜን” ሊያመጣ ወደሚችል ምዕራፍ ሁለት ይሸጋገራሉ" ብለዋል።

ስምምነቱ በባይደን እና በትራምፕ መካከል “ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ” የትብብር ደረጃ የተደረገ መሆኑም እየተነገረ ይገኛል።

ሦስት የአሜሪካ ባለስልጣናት እና አንድ የሃማስ ባለስልጣናት ስምምነት ላይ መድረሱን አረጋግጠዋል። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ፅህፈት ቤት በበኩሉ "የመጨረሻ ዝርዝሮች አሁንም ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው" ብሏል።

ስምምነቱ እስካሁን በእስራኤል ካቢኔ ያልፀደቀ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ "ሁሉም ዝርዝሮች እስካልተጠናቀቁ ድረስ በይፋ አስተያየት አልሰጥም" ማለታቸውን የሲ ኤን ኤን ዘገባ አመላክቷል።

የእስራኤል መንግሥት በዛሬው ዕለት በተደረሰው ስምምነት ላይ ድምጽ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተመላክቷል።

Post image

እስራኤል እና ሃማስ መካከል ይህ ስምምነት እንዲደረስ ኳታር፣ ግብጽ እና አሜሪካ በማደራደር እና በድጋፍ በማድረግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ተገልጿል፡፡

ይህን አውዳሚ ጦርነት ለማስቆም የተኩስ አቁም ስምምነት መደረሱን አደራዳሪዎች ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ፤ ረቡዕ ዕለት በጋዛ ሰርጥ ውስጥ በዲር አል ባላህ ጎዳናዎች እንዲሁም በቴል አቪቭ ላይ ዜጎች ደስታቸውን ሲገልጹ ተስተውለዋል።

Post image

ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው የጋዛ ጦርነት እስካሁን ከ46 ሺሕ በላይ ሰዎች በእስራኤል ዘመቻ ጋዛ ውስጥ ሲገደሉ፤ 1 ሺሕ 200 እስራኤላውያን ሞተዋል። እንዲሁም 250 የሚሆኑ ታግተው መወሰዳቸው ተገልጿል።