መጋቢት 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የጋዜጠኞች ምዝገባ፣ የሙያ ማረጋገጫ እና በብሔራዊ ሚዲያ ሽልማት እውቅና የማረጋገጫ አውደ ጥናት በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።
በዚህም በመድረኩ ላይ ጥናቱን ባደረጉ ሙያተኞች የጥናቱ ዝርዝር ጉዳይ ቀርቧል።
የመገናና ብዙሃን ጥራትን የሚያጠናክር፣ የጋዜጠኝነትን ታማኝነት የሚያረጋግጥ እና የፕሬስ ነፃነትን የሚጠብቅ ሁሉን አቀፍ አውደ ጥናት የኢትዮጵያን የሚዲያ ገፅታ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመቅረጽ አስፈላጊ ነው ተብሏል።

በዚህ አውደ ጥናት የማረጋገጫ ፕሮግራሞች በጋዜጠኝነት ሙያዊነትን፣ ተአማኒነትን እና ነፃነትን ለማጎልበት ደረጃውን የጠበቀ የእውቅና ማዕቀፍ ማቋቋምን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ተነስቷል፡፡
ይህ ማረጋገጫ ለጋዜጠኞች እውቅና ያላቸው እንዲሆኑ ያስችላል የተባለ ሲሆን፤ ፍረጃዎችን ለማስቀረት፣ ከጥቃት ለመከላከል እና ጥቃት ሲደርስባቸው ለመከላከል እና ጥብቅና ለመቆም እንደሚያስችል ተነስቷል።
ለጋዜጠኛው የተረጋገጠ መታወቂያ መስጠቱ በሙያው ላይ ጋዜጠኛ ማነው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እና በተለያዩ ፕላትፎርሞች የሚሠራውን ሁሉ ጋዜጠኛ አድርጎ የመቁጠር ችግርን ለመቅረፍ እንደሚያግዝ ተገልጿል።
እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ እየተስተዋለ ያለውን የጋዜጠኝነት ጥራትና ሥነ-ምግባር የጎደለው ሥራዎችን ለማቃናት የራሱን ሚና ይጫወታል ተብሏል።
በተመሳሳይም በፓለቲካ፣ በሀይማኖት፣ የውጭ፣ የክልል በሚል ልዩነት ያላቸውን ዘርፉ ብዙ ጋዜጠኞችን በአንድ ሙያዊ ማዕቀፍ ሥር ለመክተት አላማውን አድርጓል።
ማረጋገጫውን የሚሠጠው አካል ገለልተኛ ነው የተባለ ሲሆን፤ ማረጋጫው የህትመት፣ ብሮድካስት አገልግሎት እና ዲጂታል ሚዲያ የሚያካትት ነው።
ለዚህም ከጋዜጠኞች ጀምሮ የፎቶና ቪድዮ ጋዜጠኞች፣ አዘጋጆች፣ የዜና አርታኢ፣ ዜና አንባቢዎች፣ የሚዲያ ቴክኒሽያን ጨምሮ 14 የተለዩ መስኮች ላይ ማረጋገጫ እንደየአይነቱ ይሰጣል ተብሏል።
የቀረበው ጥናት ላይ የተለያዩ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበር፣ ኮሚኒቲ ሬድዮ፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች ጨምሮ ባለድርሻ አካላት በጥናቱ ሀሳብ ላይ አስታያየታቸውን ሰጥተዋል።
ጥናቱን በተመለከተ በርካታ ሀሳቦች የተነሱም ሲሆን፤ "መመሪያው በትኩረት ሊመለከታቸው የሚገቡ አካል ጉዳተኛ ጋዜጠኞችን እንዲሁም የዲጂታል ሚዲያን በስፋት ያላካተተ ነው" ተብሏል።
እንዲሁም በጥናቱ ላይ ግልጽ ያልሆኑ እና አሻሚ ጉዳዮች በመኖራቸው በድጋሚ መታየት እንደሚገባው ተጠቁሟል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ