መጋቢት 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሀገር ውስጥ የፈጠራ ሥራ ባለቤቶች ሥራዎቻቸውን በበቂ ሁኔታ እያስመዘገቡ አለመሆኑን የኢትዮጵያ አእምሮዊ ንብረት ባለስልጣን ገልጿል፡፡
በግንዛቤ እጥረት እንዲሁም 'የፈጠራ ሥራ ውጤቱ እንዳይሰረቅ' በሚል የተሳሳተ እሳቤ የፈጠራ ውጤቶች እውቅና እንዲያገኙ ምዝገባ እየተከናወነ አለመሆኑን፤ የባለስልጣን መ/ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኤሊያስ መሀመድ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ኃላፊው አክለውም፤ ከሀገር ውስጥ ይልቅ የውጭ ሀገር ዜጎች የፈጠራ ሥራ ውጤቶቻቸውን እያስመዘገቡ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምስረታውን ካደረገበት 1995 ዓ.ም ጀምሮ መስፈርቶችን ያሟሉ ከ30 ሺሕ በላይ የፈጠራ ሥራ ውጤቶች ምዝገባ ቢያከናውንም፤ መመዝገብ የነበረባቸው ሥራዎች በትክክል ቢመዘገቡ ቁጥሩ ከዚህ ከፍ ሊል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤቶች፣ የንግድ ምልክቶች እና የቅጅና ተዛማጅ መብት የሚያስገኙ ሥራዎች እውቅና እንዲያገኙ መስፈርቶችን መሟላታቸውን በተመለከተ ምርመራ እንደሚያከናወንም ጠቁመዋል፡፡
ከመስፈርቶቹ መካከል የፈጠራው አዲስነት እንዲሁም ማሻሻያ ከሆነ በሚቀርበው የፈጠራ ሥራ ላይ ሌላ የባለቤትነት ጥያቄ እንዳያስነሳ በነጋሪት ጋሪት ጋዜጣ ላይ ለ60 ቀናት የተቃውሞ ጥሪ እንደሚቀርብ ገልጸዋል፡፡
የዜጎች የፈጠራ ውጤች በአእምሮዊ ንብረት ባለስልጣን ምዝገባ ከተከናወነ በፈጠራዎቹ ላይ ጥበቃ የሚያገኙበት ስርዓት መኖሩን የተናገሩት ኃላፊው፤ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በተመለከተ የትብብር ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝም ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ኃላፊው ሆቴሎችም መለያቸውን በባለስልጣኑ እውቅና እንዲያገኙ ለማስቻል ምዝገባ እያከናወኑ እንዳሆነም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
"በዘርፉ ላይ የሚስተዋለውን መለያ የማመሳሰል እና የፈጠራ ውጤት ለመንጠቅ የሚደረግ ሂደት ለመከላል በባለስልጣኑ እውቅናን ማግኘት ይገባቸዋል" ብለዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የሀገር ውስጥ የፈጠራ ሥራ ባለቤቶች ሥራዎቻቸውን በበቂ ሁኔታ እያስመዘገቡ አይደለም ተባለ
