መጋቢት 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በመጋቢት ወር በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የደም ማሰባሰብ ንቅናቄ 55 ሺሕ ዩኒት ደም እንዲሁም በአዲስ አበባ ደግሞ፤ 15 ሺሕ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መታቀዱን የኢትዮጵያ የደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት አስታውቋል።
ንቅናቄው እንዲካሄድ ምክንያት የሆነው የእስልምና እና የክርስትና ተከታዮች ፆም በተመሳሳይ ወቅት ላይ መግባቱን ተከትሎ፤ የደም ለጋሽ ቁጥር ስለሚቀንስ እጥረት እንዳይፈጠር ለማድረግ በመታሰቡ ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ የደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት በፆም ወቅት ከፍተኛ የደም እጥረት እደሚገጥመው የገለጸ ሲሆን፤ ችግሩንም ለመፍታት በልዩ ትኩረት “መጋቢት ወር የደም ልገሳ ወር” በሚል ንቅናቄ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁሟል።

በመሆኑም ከዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 9 ቀን 2017 ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ መጋቢት ወር የደም ልገሳ ወር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ገልጿል፡፡
በንቅናቄው የተለያዩ ተቋማትና ማህበራት እንደሚሳተፉ የተጠቆመም ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል አቢሲኒያ ባንክ እንደሚገኝበት ተመላክቷል፡፡
በዚህም መሠረት ማንኛውም እድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ በጎ ፍቃድ ደም ለጋሽ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 54 የደም ባንክ ቅርንጫፎች ወይም ለደም ልገሳ ተብለው በሚዘጋጁ ተንቀሳቃሽ ጣቢያዎች ደም እንዲለገስ ተቋሙ ጥሪ አቅርቧል።
በፆም ወቅት የሚከሰት የደም እጥረትን ለመከላከል የሀይማኖት አባቶች እና ተማሪዎች ተባባሪ እንዲሆኑም ተጠይቋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ