መጋቢት 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከተያዘው ወር መጋቢት 6 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ትግራይ ክልል የተጫነ ነዳጅ አለመኖሩን የክልሉ ንግድና ኤክስፖርት ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው ይህን የገለጸው በነዳጅ አቅርቦት ላይ ያለው መፍትሄ ያላገኘው መስተጓገል መፍትሄ እንዲሰጥበት በመጠየቅ፤ ለፌደራል ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ለነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን እንዲሁም ለኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በትናንትናው ዕለት በጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡

በደብዳቤውም የትግራይ ሕዝብ ዕለታዊ ኑሮው የሚመራበት፣ ሁሉን አቀፍ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚያካሄድበት ብሎም ከደረሰበት ዘርፈ ብዙ ችግር ወጥቶ የዳግም ግንባታ ሥራዎች ለመስራት አስፈላጊ የሆነው ነዳጅ ወደ ትግራይ ክልል ከወርሃ ጥር 2017 ዓ/ም መጠኑ እጅጉን የቀነሰ መሆኑን በማንሳት፤ መፍትሄ እንዲሰጥበት በተደጋጋሚ ሲጠይቅ መቆየቱን ገልጿል፡፡

Post image

ነገር ግን "ለረጅም ጊዜ በክልሉ የሚገባው የነዳጅ መጠን መቀነሱ ሳይበቃ፤ ባለፉት 10 ቀናት ሙሉ በሙሉ ወደ ትግራይ የሚጫን ነዳጅ ቆሟል" ብሏል።

ይህም እንደ ክልል የሰብዓዊና እርዳታ ሥራዎች የሆስፒታሎችና አምቡላሶች ሥራ፣ የመድኃኒት አቅርቦትና ስርጭት ሥራ ላይ መስተጓጐል ማስከተሉን አስታውቋል።

በተጨማሪም የነዳጅ አቅርቦት መቋረጡ በክልሉ በሚገኙ የተፈናቃይ መጠለያ ማዕከላት የምግብና መድሃኒት አቅርቦት ሥራዎች፣ የመስኖ ልማት፣ የአውሮፕላንና የየብስ ትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች እንዲሁም የመንግሥትና የልማት ሥራዎች እንዲቆሙ ማድረጉን ገልጿል፡፡

Post image

ይህም በአጠቃላይ የትግራይ ሕዝብ ሁሉን አቀፍ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከነበረበት ችግር በባሰ መልኩ ወደ አደጋ ያመራበት ሁኔታ መኖሩን የገለጸም ሲሆን፤ የፌደራል ተቋማቱ ይህን ተገንዝበው ሕዝቡን ከዚህ ችግር እንዲላቀቅ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ