ጥር 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ አየር ሃይል ዋና አዛዥ የሆኑት ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ እና ሌሎች ከተቋሙ የተውጣጡ ልዩ አመራሮች እና አባላት ለመቄዶንያ ከ2 ሚልየን ብር በላይ የሚገመት የምግብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።
አመራሮቹ በአዲስ አበባ አያት ፀበል አካባቢ በሚገኘው የመቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር በመገኘት ነው በዛሬው ዕለት ድጋፉን ያደረጉት።
በተጨማሪም አዛዡና አመራሮቹ መቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፤ በማህበሩ አጠቃላይ ሥራ ዙሪያ የተዘጋጀውን ዶክመንተሪም ተመልክተዋል።
መቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር ምንም ደጋፊና ጧሪ የሌላቸውን በተለይም ደግሞ እራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ፣ መመገብ እና መፀዳዳት የማይችሉ የአልጋ ቁራኛ የሆኑና የሰው ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አረጋውያንንና አዕምሮ ሕሙማንን ከወደቁበት ጎዳና ላይ በማንሳት ከ8 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ተረጂዎች የሚገኙ ሲሆን፤ ተቋሙ በበጎ ፍቃደኞች ድጋፍ ብቻ እንደሚንቀሳቀስም ተነግሯል፡፡
አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ አደዋ፣ ሐረር፣ ጎሬ፣ ሰንዳፋ፣ ሐዋላ፣ አሶሳ፣ ሞያሌ፣ ያቤሎ፡ ምንጃር፣ ጎንደር፣ ደብረማርቆስ፣ አምቦ፣ ጂማ፣ ኮረም፣ ሰመራ፣ ሰቆጣ፣ ደባርቅ፣ ዓዲግራት፣ ነገሌቦረና፣ ኮንሶ፣ ሰላድንጋይ (ፃድቃኔ ማርያም)፣ አምደወርቅ፣ ላሊበላ፣ መቱ፣ አዲስ ዘመን እና አርባምንጭን ጨምሮ በአጠቃላይ በ44 ከተሞች ውስጥ እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በቀጣይም ወሊሶ፣ በሱልልታ፣ ሰበታ፣ ደብረ ብርሃን፣ ሆሳዕና፣ ዲላ፣ ጂግጂጋ እና በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞችን ለመስራት ከወዲሁ እንቅስቃሴ መጀመሩም ተነግሯል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ