ጥር 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በተለያዩ ማሕበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት "የብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎትን መንግሥት ግለሰባዊ ማንነቶች በመለየት ዜጎችን ከሕግ አግባብ ውጭ ለማጥቃት ታሳቦ የጀመረው አገልግሎት ነው" ተብሎ የሚሰራጩ መረጃዎች የተዛቡና የተሳሳቱ አመለካከቶች ናቸው ሲል የዲጅታል መታወቂያ ፕሮግራም አገልግሎት ለአሐዱ አስታውቋል።
ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ውስጥ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ቃልኪዳን አብርሃም፤ ዲጂታል መታወቂያ የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ያስችላል ብለዋል።
ዜጎች ከመንግሥት ተቋማት አገልግሎትን በፍትሐዊነት እንዲያገኙና የተለያዩ ወንጀሎችን በተለይም የሳይበርና የማጭበርበር ወንጀሎችን ለመቀነስ ትልቅ ሚና እንዳለውም አንስተዋል።
የዲጂታል የመታወቂያ ሥርዓት የባዮሜትሪክ መረጃን በመጠቀም ለሁሉም አገልግሎት ሰጪዎች ማንነትን በማረጋገጥ እና በኤሌክትሮኒክ መልኩ ደንበኞቻቸውን ማወቅ የሚያስችል ሀገር አቀፍ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት መሆኑን አብራርተዋል።
"በዚህ ረገድ የሚዛቡ መረጃዎችም ከግንዛቤ ዕጥረት የተነሳ የመጡ ናቸው" ብለዋል።
አያይዘውም ፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ የተደራጀ የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት አገልግሎት አሰጣጥን የሚያዘምን ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል።
በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ከ70 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት የሚሆንበት የምዝገባ ሥራ መጀመሩንም የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዋ አስታውሰዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ