ጥር 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት አንዱ የሆነውና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ የተመዘገበው የጥምቀት በዓል በድምቀት ተከብሮ ውሏል።
በዘንድሮ የጥምቀት በዓልም በርካታ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች የተገኙበት እንደሆነ የቱሪዝም ሚኒስቴር ለአሐዱ አስታዉቋል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር የኮምኒኬሽን እና የሕዝብ ግኝኑነት ሥራ አስፈጻሚ አቶ አለማየሁ ጌታቸው፤ የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች በአክሱም፣ ባቱ እና ላሊበላን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መገኘታቸውን ገልጸዋል።
እንዲሁም "የዓለም አቀፍ ኮንፍረንስን ለመሳተፍ የመጡ መስማት የተሳናቸው ዜጎች በጥምቀት በዓሉ ላይ ተሳታፊ ነበሩ" ብለዋል።
የጥምቀት በዓል ከመንፈሳዊና ባህላዊ ክንውኑ ባሻገር በሥነ-ስርዓቱ ለመታደም የሚመጡ ቱሪስቶች በቆይታቸው መጠን የገቢ ምንጭ በመሆን የራሳቸውን ሚና እንደሚጫወቱም ጠቁመዋል።
"በዓሉ በአጠቃላይ በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢ በድምቀት ተከብሯል" ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፤ "ከዋዜማው ጀምሮ እስከ ቃና ዘገሊላ ዕለት ድረስ ደማቅ በዓል ነው" ሲሉ አንስተዋል።
እንዲሁም በዚህ ዓመት ለበዓሉ የተሰጠው ሽፋን ከሌላ ጊዜው እጅግ የጎላ መሆኑ ገልጸው፤ ከዚህ በፊት የማይታወቁ አካባቢዎችን ብሎም በሌላው ዓለም የነበረው ሥነ-ስርዓትም የሚዲያ ሽፋን ማግኘቱን አመላክተዋል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር ስለ ጥምቀት በዓል ሰፊ የሆነ የማስተዋወቅ ሥራዎችን መስራቱን የገለጹ ሲሆን፤ "በዓሉ የሀገር ገጽታ ላይ ሰፊ የሆነ ድርሻ አለው" ሲሉ ተናግረዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ