ጥር 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ ምንም አይነት እውቅናን ሳያገኙ ከሕግ ውጪ በመደራጀት የፓርኪንግ አገልግሎትን የሚሰጡ ማህበራት በብዛት መኖራቸውን፤ የከተማ አስተዳደሩ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ ለአሐዱ ተናግረዋል።

ሕገ-ወጥ የፓርኪንግ አገልግሎት ላይ የተደራጁ ማህበራት ወደ ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲመጡ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በጋራ እየተሰራበት መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት በቅርብ ጊዜ ውስጥ በተሰራ ሥራ ከ30 በላይ ሕገ-ወጥ የፓርኪንግ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ማህበራት ወደ ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲመጡ መደረጉን አስረድተዋል።

ሕጋዊ ሆነው የሚሰሩ ማህበራትም መንግሥት ባወጣው ታሪፍ መሰረት ሲሰሩ እንዳልነበር አስታውሰዋል።

ለፓርኪንግ አገልግሎት ሕጋዊ እውቅና የተሰጣቸው እና ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ጋር ውል ገብተው በመስራት ላይ የሚገኙ ከ13 ሺሕ በላይ ወጣቶችና ሴቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

አክለውም በርካታ አሽከርካሪዎች ለፓርኪንግ አገልግሎት የማይከፍሉ ስለመኖራቸውም አንስተዋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አሽከርካሪዎችም ሆነ የፓርኪንግ በአገልግሎት ሰጪዎች በኩል ያለውን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም ባሻገር፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በመስራት ሕገ-ወጥ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ማህበራትን ወደ ሕጋዊ ማዕቀፍ የማምጣቱን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን የከተማዋን የትራፊክ ቁጥጥር እና ፓርኪንግ አስተዳደር ሥርዓት ከማንዋል ወደ ዲጂታል የሚያሸጋግር ሶፍትዌር አበልፅጎ ለትግበራ ማብቃቱ ይታወሳል።

በዚህም በከተማዋ የትራፊክ ደንብ የተላለፉ አሽከርካሪዎች የቅጣት ክፍያቸውን እንዲሁም የፓርኪንግ አገልግሎት ክፍያቸውን ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የሚከፍሉበትን አሠራር ስለማስጀመሩም አሐዱ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡