ጥር 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የጸጥታ አካላትን ጨምሮ የዞን እና የከተማ አመራሮች፣ የነዳጅ ማደያ ሠራተኞች፣ የሞተር ሳይክል እና ባለሦስት እግር ተሸከርካሪ ሾፌሮች እየተሳተፉበት የሚገኘውን ሕገ-ወጥ የነዳጅ ንግድ ለመቆጣጠር አዲስ የ"ኩፖን" አሰራር መዘርጋቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ንግድ ቢሮ አስታውቋል።
በዚህም መሠረት በክልሉ ከጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የቤንዚን ሽያጭ ሕጋዊ ሰሌዳ ላላቸው ተሽከርካሪዎች በኩፖን ብቻ እንዲከናወን ውሳኔ መተላለፉ ገልጿል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሳሙኤል ሳዲሁን፤ በአዲሱ አሰራር አማካኝነት አሽከርካሪዎች አስቀድሞ በሚሰጣቸው የነዳጅ ደንበኝነት ደብተር (ኩፖን) መሰረት በተመደቡላቸው ነዳጅ ማደያ ቅርንጫፎች እና በተሽከርካሪዎቻቸው ብቻ ነዳጅ እንዲቀዱ እየተደረገ እንደሚገኝ ለአሐዱ ተናግረዋል።
ኩፖን የሚሰጠው የተሽከርካሪው ዓይነት፤ የታርጋ ቁጥር እና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን በማስመዝገብ እንደሆነም ተነግሯል።
ንግድ ቢሮው የተከተለው አዲሱ አሰራር በበቂ መጠን እየቀረበ የሚገኘው ነዳጅ የግለሰቦች መጠቀሚያ እንዳይሆን ማድረጉን ያነሱት ምክትል ኃላፊው፤ "ማኅበረሰቡ የነዳጅ ምርቶችን ከመደበኛ ዋጋው በላይ በከፍተኛ ጭማሪ እንዳይገዛ አድርጓል" ብለዋል።
ኃላፊው "ዘመናዊ" ሲሉ የጠሩት በኩፖን የታገዘ አሰራር ሀሰተኛ ማስረጃዎች ግልጋሎት ላይ እንዳይውሉ፣ ሕገ-ወጥነት እንዳይኖር፣ ነዳጁ ከተቀመጠለት ታሪፍ በላይ እንዳይጥል እንደሚያደርግ ታምኖበታል።
አዲሱ የነዳጅ ሽያጭ መላ ለሕገ-ወጥ አሰራር ተጋላጭ እንዳይሆን የቁጥጥር ኮሚቴ እንደተቋቋመለትና ኮሚቴው የቅርብ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ተነግሯል።
አሐዱ በክልሉ የሚገኘውን የነዳጅ አቅርቦት ችግርና በሕገ-ወጥ መንገድ በሊትር ከ400 እስከ 500 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ መዘገቡ የሚታወስ ነው።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ