ጥር 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስልጤ ዞን በከባድ የሰው መግደል ወንጀል በተከሰሱ በሦስት ግለሰቦች ላይ የስልጤ ዞን ከፍተኛ ፍርድና ቤት የሞት ፍርድ ውሳኔ አስተላልፏል።
በዞኑ ስልጢ ወረዳ በሰነና ገሬራ ቀበሌ መንደር ሁለት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ከረፋዱ 4:00 አካባቢ እጅግ ነውረኛና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ግድያ መፈፀሙ ተገልጿል።
ወንጀሉም አባት ከሁለት ልጆቹ ጋር በመሆን ከገዛ ልጃቸው መካከል አንዱ በሆነው ዋሲጥ ሙስጠፋ ላይ መፈፀሙን የስልጤ ዞን ፖሊስ መምሪያ ሕዝብ ግንኙነትና ሚድያ ጉዳዮች ድቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ከድር ኤርጎሻ ለአሐዱ ተናግረዋል።
ድርጊቱን 1ኛ, ሙስጠፋ ደልዋቶ የሟች አባት 2ኛ,ሙዲን ሙስጠፋ የሟች ወንድም እና 3ኛ,ሸምሱ ሙስጠፋ የተባሉ ተከሳሾች ለጊዜው ካልተያዘ የሟች ወንድም ጋር በመሆን በመሬት ምክንያት በቂም በቀል ተነሳስተው መፈፀማቸው ተገልጿል።
ስለሆነም መረጃው የደረሰው የስልጢ ወረዳ ፖሊስ በወቅቱ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ መጀመሩ ተነግሯል።
በመቀጠልም የሰውና የሰነድ ማስረጃ በመሰባሰብ ምርመራውን አጠናቆ መዝገብ በማደራጀት ለስልጤ ዞን ፍትህ መምሪያ ዐቃቤ ሕግ መላኩን ኮማንደር ከድር አክለዋል።
የስልጤ ዞን ዓቃቤ ህግ በበኩሉ ከፖሊስ የቀረበለትን መዝገብ በማየት በሦስቱም ተከሳሾች ላይ በፈፀሙት ከበድ የሆነ የሰው ግድያ ወንጀል ክስ በመመስረት ለስልጤ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል።
የስልጤ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከዐቃቤ ሕግ የቀረበለትን ክስ በማየት ከመረመረ በኋላ ተጠርጣሪዎች ወንጀል መፈፀማቸውን በሰውና በሕክምና ሰነድ ማስረጃ በማረጋገጥ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የጥፋተኝነት ብይን ሰጥቷል።
የስልጤ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥር 14 ቀን 2017 ዓ. ም በዋለው የወንጀል ችሎት ተከሳሾችን ያርማል ሌሎች መሰል ድርጊት የሚፈፅሙ አካላትን ያስተምራል በማለት ሦስቱንም ተከሳሾች በሞት እንዲቀጡ ውሳኔ ሰጥቷል።
በተጨማሪም 3ኛ ተከሳሽ ሻምሱ ሙስጠፋ በሕግ ቁጥጥር ሥር ያልዋለ በመሆኑ፤ ፖሊስ ተከሳሽን በተገኘበት አፈላልጎ በቁጥር ሥር በማዋል አስሮ ለወራቤ ማረሚያ ተቋም እንዲያስረክብ ፍርድ ቤቱ አዟል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ