ታሕሳስ 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የትራፊክ ቅጣትንና የፓርኪንግ ክፍያን የሚያዘመን እና መሰረታዊ የሆኑ ግብዓቶች የተሟሉት መተግበሪያ በልጽጎ ወደ ሥራ መግባቱን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን አስታውቋል።
"ለአገልግሎቱ የሚውል የሰርቨር እና ታብሌቶች ግዢ ተፈጽሟል፣ መተግበሪያም በልጽጓል" ያለው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፤ ከኢንፍራ ቴክ ሶፍትዌር አበልጻጊ ድርጅት ጋር በመተባበር የተሰራውን መተግበሪያ ከቴሌብር እና ከባንኮች ጋር የማስተሳሰር ሥራው ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁን ገልጿል።
ከዚሁ ጋር በተያያዝም በመንገድ ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ 395/2009 ላይ የነበሩ ክፍተቶችን እና እንደ አዲስ መካተት ያለባቸውን በጥናት እና ባለድርሻ ተቋማትን ባሳተፈ መልኩ በመለየት፤ ደንብ 557/2016 በማጸደቅና ከሲስተም ጋር በማቀናጀት ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆኑን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክበበው ሚደቅሳ ገልጸዋል፡፡
ሲስተሙ በዋናነት ቀደም ሲል በማኑዋል ሲሰሩ የነበሩ አንዳንድ የቁጥጥር ብልሹ አሰራራሮችን የሚያስቀር መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ለትራፊክ ቅጣት ፓድ ህትመት ብቻ የሚወጣውን በዓመት ከ17 ሚልዮን ብር በላይ ወጪ ያድናልም ተብሏል።
በተጨማሪም የትራፊክ ደንብ ተላላፊዎች ታርጋ ሲፈታ እና መንጃ ፈቃድ ሲወሰድባቸው መልሰው ለመውሰድ የነበረውን ውጣ ውረድ፣ የሚያስቀርና በአጠቃላይ ከደንብ መተላለፍ የእርምት እርምጃ አወሳሰድ ጋር የነበሩ ሰው ሰራሽ ችግሮችን የሚቀርፍ መሆኑ ተነግሯል።
እንዲሁም ሲስተሙ የፓርኪንግ አገልግሎት ክፍያ ጋርም የሚያያዝ በመሆኑ ቀደም ሲል በአገልግሎቱ ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችንም የሚፈታ እንደሆነ ተገልጿል።
በዚህም በአዲሱ የትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ መሠረት፤ ለመጀመሪያ ደረጃ እርከን ጥፋቶች ከ500 ብር ጀምሮ ለሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ እርከኖች ከ1 ሺሕ 500 እስከ ሦስት ሺሕ ብር ድረስ ቅጣት የሚጥል መሆኑ ተነግሯል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በዓመት ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የደንብ መተላለፎች እንደሚከሰቱ ባለስልጣኑ የገለጸ ሲሆን፤ 52 በመቶ የሚሆኑት ተሽከርካሪዎች ከፍጥነት በላይ እንደሚያሽከረክሩ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በዚህም ምክንያት በከተማዋ በትራፊክ አደጋ ብቻ በዓመት ከ300 እስከ 400 የሚደርሱ ሰዎች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ተገልጿል፡፡
የትራፊክ ቅጣትንና የፓርኪንግ ክፍያን የሚያዘምን ሶፍትዌር ወደ ሥራ ሊገባ መሆኑ ተገለጸ
ጥፋት በሚፈጽሙ አሽከርካሪዎች ላይ ከ500 ብር እስከ ሦስት ሺሕ ብር የሚደርስ ቅጣት ይጣላል ተብሏል