ጥር 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) መንግሥት የሰላም አማራጭን በመቀበል ለሚገቡ የትኞቹም ቡድኖች ዛሬም በሩ ክፍት ነው፡፡ ለዚህም ጥሪውን በድጋሚ ያስተላልፋል ሲሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በሀገሪቱ ያለፉ ቁርሾዎችንና ስብራቶችን የሚጠግን፣ በትብብር ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ባህልን የሚያጎለብት መደላድል እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"የሰላምን አማራጭ የተከተሉ የትኞቹም ቡድኖች በሀገረ መንግሥት ግንባታ ጥረት በንቃት እንዲሳተፉና የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ጽኑ ፍላጎት አለው" ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ለሰላም አዎንታዊ ምላሽ የሰጡ የቀድሞ ታጣቂዎች ሀገሪቱ በያዘችው የሰላምና የብልጽግና ጉዞ ሂደት ውስጥ ሊጫወቱ የሚችሉትን ወሳኝ ሚና መንግሥት ይገነዘባልም ብለዋል፡፡

"የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሉንም ወገኖች የሚያሳትፍና የሚያግባባ፣ አብሮነትን የሚያጎለብት፣ ብዝኃነትንና አንድነትን የሚያሳልጥ፣ በብሔራዊ ትርክት ላይ የተመሰረተ ሀገረ መንግሥት ለመመስረት ጥረት እያደረገ ይገኛል" ነው ያሉት።

"ነጻ፣ ገለልተኛና ብቃት ያላቸው ተቋማትን በመገንባት ትውልድ ተሻጋሪና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ዘርፈ ብዙ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፤ በዚህም አበረታች ውጤት እየተገኘበት ነው" ሲሉም ገልጸዋል።

"ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ ለመፍታት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአብዛኞቹ የሀገራችን ክልሎች ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመምከር አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ሥራ አከናውኗል" ብለዋል።

"በቀሪዎቹ የአማራና የትግራይ ክልሎችም ተመሳሳይ ሥራ ለመስራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠረ ይገኛል" ማለታቸውን ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተጨማሪም "መንግሥት ሰላምና መረጋጋትን በመፍጠር የዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ የጀመረውን ሁሉን አቀፍ ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል" ያሉት ሚኒስትሩ፤ ዜጎችም እንደተለመደው የድርሻቸውን ኃላፊነት መወጣት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ