ጥር 9/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኮንትሮባንድ፣ የድንበር ላይ ጥበቃ፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን እንዲሁም የከተማ ውስጥ ፀጥታ ቁጥጥር ሥራዎችን በብቃት ማከናወን የሚያስችል የድሮን ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ሊያውል መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በዋናው መስሪያ ቤት የተደራጀውን የድሮን ፓይለት ማሰልጠኛ ማዕከል (UAV Simulation Training Center) በትናንትናው ዕለት መርቀው ሥራ ያስጀመሩ ሲሆን፤ የድሮን ቴክኖሎጂው በተቋሙ ላለው የወንጀል መከላከል ሰርቪላንስ እና የምርመራ ሥራ ከፍተኛ እገዛ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽነር ጀነራሉ አክለውም፤ "የሪፎርሙ መንግሥት ለፖሊስ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ፖሊስ ዘመናዊ ትጥቆች እንዲኖሩትና ሰብዓዊ መብትን ባከበረ መልኩ የወንጀል መከላከልና የምርመራ ሥራዎቻችን መስራት በሚያስችል መልኩ አቅሙን እያሳደገ ነው" ብለዋል፡፡
"አዲስ ያስገባናቸው ድሮኖች ከከተማ ፀጥታ ቁጥጥር ባሻገር የድንበር ጥበቃን ጨምሮ የኮንትሮባንድ እና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በቀላሉ መቆጣጠር የምንችልበትን ዕድል የሚፈጥሩልን ይሆናል" ሲሉም ተናግረዋል።
"በፖሊስ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ፖሊስ በዘመኑ እንደዚህ አይነት ቴክኖሎጂዎችን ታጥቆ አያውቅም ያሉት" ኮሚሽነር ጀነራሉ፤ "የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በሪፎርሙ አሁን ላይ ከአፍሪካ አምስቱ ምርጥ የፖሊስ ተቋማት ውስጥ ለመግባት እያደረገ ያለውን ጥረት በሚያግዝና ለአፍሪካ ወንድሞቻችንም ልምድ እና ተሞክሮ ማስተላለፍ በሚያስችል መልኩ እየተደራጀ ነው" ብለዋል፡፡
እንደ አዲስ አበባ ያሉ ትላልቅ ከተሞችን ፓትሮል ለማድረግ የእግረኛ ፖሊስ ሠራዊትን ከድሮን ፓትሮል ጋር በማቀናጀት እና በማዋሀድ የወንጀል መከላከል ስራችንን እያቀላጠፍን የምንሰራበት እድል ከመፍጠር ባለፈ አድማዎች ሲያጋጥሙ በተደራጀና በጠንካራ ሠራዊታችንና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዘን በቀላሉ ችግሮችን መቆጣጠር የሚያስችል አቅም ፈጥረናል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም እንደ አፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ያሉ መድረኮች ሲኖሩ ለተወሰነ ጊዜ መንገዶችን ዘግቶ ቪአይፒዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል፤ የራሱ የሆነ ኮማንድ ኮንትሮል ያለው ዘመናዊ Road block ተሸከርካሪም ተመርቆ ሥራ እንዲጀምር መደረጉን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ