መጋቢት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎችን መንግሥት በአፋጣኝ ወደቀያቸው መመለስ እንደሚገባው የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ትግራይ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አሳስቧል።

በክልሉ ከሱዳንና ጠለምት ወረዳ ተመልሰው የመጡትን ሳይጨምር 970 ሺህ አካባቢ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የገለጹት የጽ/ቤቱ ኃላፊ ፀሀዬ እንባየ፤ በቂ ድጋፍም እየተደረገላቸው አለመሆኑን ለአሐዱ በሰጡት ቃል አስታውቀዋል።

የመጠለያ ድንኳንም ከተሰራ ሦስትና አራት ዓመት አስቆጥሮ ያረጀ በመሆኑ፤ በጨርቅና ላስቲክ ሸፍነው እየተጠቀሙ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

አክለውም "የተፈናቃዮች አለመመለስ በትምህርት ስርዓቱና ሌሎች ማህበራዊ ሕይወቶች ላይ ችግር እየፈጠረ በመሆኑ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት አለበት" ብለዋል።

በመሆኑም ይህ ሁሉ ችግር ሊቀረፍ የሚችለው ግን ወደ ቀያቸው መመለስ ሲችሉ ብቻ እንደሆነ አፅንኦት ሰጥተዋል።

አሐዱም "የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (USAID) እርዳታ ማቋረጡን ተከትሎ በተለይም ተፈናቃዮች ላይ ምን አይነት ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል?" ሲል የጠየቀ ሲሆን፤ ኃላፊው በምላሻቸው ቀድሞውኑ የነበረው ችግር እየተባባሰ እንደሚሄድ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በእርዳታ ሰጪዎች አማካኝነት ለጥቂቶች ብቻ ድጋፍ ሲደረግ ለብዙሃኑ እንደተደረገ ተደርጎ መረጃ ስለሚሰራጭ ይሄ በራሱ ተፈናቃዮች ላይ ጫና ሲፈጥር የቆየ መሆኑን በማንሳት፤ በውጪ እርዳታ ተመርኩዞ የሚደረግ ድጋፍ ዘላቂ ስለማይሆን ዋነኛው መፍትሄ መንግስት በራሱ አቅም ማገዝ ሲችል እንደሆነም ኃላፊው ጨምረው ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ