መጋቢት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በምሽት የንግድ እና የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ የወጣው ደንብ ቁጥር185/2017 ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን አስታውቋል።
ቢሮው የአዲስ አበባ ከተማ አሁን ከደረሰችበት ኢኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ለውጥ አንፃር የአብዛኛው ማህበረሰብ የሥራ ባህል እና ፍላጎት በመለወጡ የንግድ ሥራዎችንና አገልግሎቶችን በምሽት መከወን እየተለመደ የመጣውን ተግባር ወጥነትና ቀጣይነቱን ማረጋገጥ ማስፈለጉን ገልጿል።
በዚህም መሠረት በከተማዋ በቀን ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ በምሽት የንግድ እና አገልግሎት መስጫ ተቋማት አገልግሎት የሚሰጡበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ደንቡ መውጣቱን የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ሐቢባ ሲራጅ ተናግረዋል።

ይህ ደንብ ቀደም ብሎ በከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ያስተላለፈውን ውሳኔ ለማስፈጸም በመሆኑ ከዛሬ መጋቢት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን አስታውቀዋል።
በዚህም በደንቡ የተካተቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ማብራሪያ በሁሉም የሚዲያ አውታሮች አማካኝነት ማህበረሰቡ እንዲያውቃቸው እንደሚደረግ እና ደንቡን የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሰራም ወ/ሮ ሐቢባ አክለው ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ