መጋቢት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ቦርን አጌን የአእምሮ ጤና ማገገሚያ እና የፈውስ ማዕከል በማዕከሉ ውስጥ ላሉ ታካሚዎች መድኃኒት ለማግኘት ተቸግሪያለሁ ሲል ለአሐዱ ገልጿል፡፡
የማዕከሉ መስራች እና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ኪያ ስብሃት መድኃኒቱ የሚገኘው ከአማኔኤል ሆስፒታል እንደሆነ አንስተው፤ በግዥ ወቅት ከፈተኛ የሆነ እንግልት እየገጠማቸው በመሆኑን ተናግረዋል፡፡
ማዕከሉ በአሁን ጊዜ ከ122 በላይ የአእምሮ ሕሙማንን የእዕምሮ ሕሙማንን ከጎዳና ላይ በማንሳት ከአእምሮ ሕመማቸው እንዲያገግሙ በመደገፍ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ወ/ሮ ኪያ፤ 23 የሴት የአእምሮ ሕሙማን ልጆችን በማሳደግ ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡
በዚህም በማዕከሉ ሕክምናን ጨምሮ የተለያዩ እርዳታዎችን የሚሹ ዜጎች በመኖራቸው፤ በአማኑኤል ሆስፒታል ያለው የአሰራር ስርዓት እንዲስተካከል እና ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ጠይቀዋል፡፡
አሐዱም የተነሳውን ቅሬታ መሠረት በማድረግ የአማኑኤል ሆስፒታል የመድኃኒት ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ አበራ ገላን ጠይቋል፡፡
በምላሻቸውም የመድኃኒት እጥረት በመኖሩ ለግል ድርጅቶች መስጠት እንዳልተቻለ እና ለ1 ወር ወይም ለ2 ወር መድኃኒቱ ላይገኝ እንደሚችል በማንሳት ችግሩ እንዳለ አረጋግጠዋል፡፡
አስቀድሞ በሆስፒታሉ ለሚታከሙ ሕሙማን መድኃኒት መሰጠት እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ አበራ፤ የመድኃኒት እጥረቱን በተመለከተ ለኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ጥያቄ ማቅረባቸውንም ተናግረዋል፡፡
የአማኑኤል ሆስፒታል ከመድኀኃኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ያነሳውን ችግር በተመለከተ አሐዱ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ጠይቋል፡፡
ምላሽ የሰጡት የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አወል ሀሰን፤ የሆስፒታሉን የመድኃኒት እጥረት ለመፍታት 48 ሚሊዮን ብር የሚገመት መድኃኒት ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን ተናግረዋል፡፡
218 የተለያዩ መድኃኒቶች ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን እና ባለፈው ሳምንት ለሆስፒታሉ ማስረከቡንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ከመድኃኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘ የአቅርቦት ችግር፣ ተቋማት ተናበው አለመስራታቸው፣ ሕገ-ወጥ አሰራር መኖሩ ተግዳሮት እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገለጽ የሚሰማ ሲሆን፤ ይህም ተገልጋዮችን ለእንግልት እየዳረገ በመሆኑ መፍትሄ መስጠት ከባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ነው፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ማዕከሉ የመድኃኒት እጥረት ገጥሞኛል ሲል ገለጸ
