መጋቢት 11/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በቡና መገኛነቷ የምትታወቀው ኢትዮጵያ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያው የምታቀርበው ምርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢሆንም፤ እሴት በመጨመር፣ የተቀባይ ሀገራትን የጥራት ደረጃ እና ፍላጎት በማሟላት ዘርፉ ማግኘት የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ እንዳያስገኝ የፋይናንስ እና የቦታ እጥረት እንቅፋት እንደሆኑ የኢትዮጵያ የቡና ቆይዎች ማኅበር አስታውቋል፡፡

የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ አሰፋ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ አበዳሪ ተቋማት ዘርፉን ለመደገፍ ያላቸው ፈቃደኝነት ማነስ በተለይም ቡናን ቆልቶ፣ ፈጭቶና አሽጎ ለውጭ ገበያ ለማቅረብና በዓለም አቀፉ መድረክ ተወዳዳሪ ለመሆን እንዳይቻል እንቅፋት ሆኗል።

የኢትዮጵያ ምርት በዓለም ያለውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እንቅፋት ናቸው ያሏቸውን ምክንያቶች የዘረዘሩት የቡና ቆይዎች ማኅበር ፕሬዝዳንቱ፤ "ሁሉም ባድርሻዎች የዘርፉን ችግሮች ለመቅረፍ ያላቸው ፈቃደኝነት አበረታች አይደለም" ብለዋል።

ማኅበሩ የሀገሪቱን የቡና ዘርፍ ለመደገፍ የፋይናንስ አቅርቦትን በማሻሻል እና የተሻለ መሠረተ ልማት በማሟላት ረገድ የሚመለከታቸው አካላት እና ባለድርሻ አካላት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ