መጋቢት 11/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው ዕለት ከሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፤ "የባህር በር ጥያቄን ማንሳት ነውርነቱ አብቅቷል፡፡ ብልጽግና ኖረም አልኖረም የባህር በር ፍላጎት እና ጥያቄ ሁሌም ያለ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

"የቀይ ባህር ፍላጎታችን ከሶማሊያም፣ ከጀቡቲም፣ ከኬንያም የሚያጣላን አይደለም፡፡ የተገደበም አይደለም፡፡ የሚመለሰው ግን በውይይት መሆን አለበት" ሲሉ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከሰሞኑ ከኤርትራ ጋር ግጭት ይነሳል የሚል ስጋት እየተንጸባረቀ መሆኑን አስታውሰው፤ "መንግሥት ለቀይ ባህር ሲል ኤርትራን የመውረር ፍላጎት የለውም፡፡ ፍላጎታችን መነጋገር ነው" ብለዋል፡፡

"ኢትዮጵያ ለቀይ ባህር ስትል ኤርትራን የመውረር ፍላጎት የላትም" በማለት የመንግሥትን ወቅታዊ አቋም የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዓለም ሀገራት የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ስለማመናቸው አብራርተዋል፡፡

የትኛውም ዝግጅቶች ውግያን ለማስቀረት ታስበው የሚደረጉ መሆናቸውን አንስተው፤ "ከጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ጋር የተገኘው ዲፕሎማሲያዊ ድል ለዚህ ማሳያ ነው" ብለውታል፡፡

"ከጀመርነው ሕልማችን የሚያስቆመን ኃይል አለ ብለን አናምንም" ያሉም ሲሆን፤ "ትንኮሳ ካለ ግን ምላሹ የከፋ ይሆናል" ብለዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ