መጋቢት 11/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) መጋቢት 4 ቀን 2003 ዓ.ም የተጀመረው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላለፉት 15 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ የግንባታ ሥራው ሲከናወን ቆይቷል።

15 ዓመታትን ሊደፍን የቀናት ዕድሜ የቀሩት ግድቡ በመጪው መስከረም ወር እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

ይህ የተገለጸው ጠቅላይ ሚንስቴር ዐቢይ አሕመድ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የአፈጻጸም ሪፖርት መነሻ በማድረግ፤ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው።

እንደጠቅላይ ሚንስትሩ ገለጻም፤ "በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ሪቫን ቆርጠን ታሪክ እናደርገዋለን" ብለዋል።

አክለውም ከግብጽ ጋር ባለው ሁኔታ ከግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራን የደህንነት ሹም ጋር ከአንዴም ሁለት ጊዜ ንግግር ማድረጋቸው አንስተዋል።

Post image


የሕዳሴ ግድብ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተለይም በግብጽ ላይ የሚያመጣው ችግር የለም ያሉ ሲሆን "እንሱን መጉዳት አንፈልግም ስጋታቸው ድርቅ ቢመጣስ የሚል ቢሆንም አባይ መነሻውን ከኢትዮጵያ በማድረጉ ለነሱ ስጋት የሚሆን ነገር የለውም" ብለዋል።

"ለፕሬዝዳንት አል ሲሲ በገባነው ቃል፤ ሕዳሴ ሲሞላ ከአስዋን ግድብ አንድም ሊትር ውሃ አይቀንስም ባልነው መሐረት የሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ተጠናቆ። ከግብጽ ላይ ምንም ውሃ አልቀነሰም" ሲሉም ገልጸዋል።

ከዚህ በኅላም ከግብጽ ጋር ውይይት በማድረግ የሁለቱንም ሕዝቦች ተጠቃሚ ለማድረግ መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።

እንዲሁም "ለንግግር፣ ለውይይት እና የሕዳሴ ግድብን ለማስጎብኘት የኢትዮጵያ በር ክፍት ነው" ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ