ጥር 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ከሰሞኑ በክልሉ ከፍተኛ የጦር አዛዦች የተላለፈው መልዕክት ወደ ዳግም ጦርነት የሚያስገባ እንዳይሆን ስጋት እንዳለው ለአሐዱ ገልጿል።
ከሰሞኑ በትግራይ ክልል ከፍተኛ ወታደራዊ ኃይል አመራሮች የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደ አዲስ እንዲዋቀር ውሳኔ ማሳለፋቸውን መግለፃቸው ይታወሳል።
ይህንን የወታደራዊ አዛዦች መግለጫም ተከትሎ የጊዚያዊ አስተዳደሩ ረዘም ያለ መግለጫ የሰጠ ሲሆን፤ "በግልፅ ለአንድ ቡድን የወገነና የፕሪቶሪያውን ውል የሚጥስ መግለጫ ነው" ሲል ገልጾታል።
አሐዱም ይህንን በክልሉ እየተካረረ የመጣውንና ከፍተኛ ስጋት የደቀነውን ጉዳይ በተለመለከተ የቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር መብሪህ ብርሀኔንን "አሁን ያለዉ ሁኔታ አሳሳቢነቱ ምን ያህል ነው?" ሲል ጠይቋል።
በምላሻቸውም አሁን ያለዉ ሁኔታ አስቸጋሪ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ "ከሕግ አንፃርም ቢሆን መሰረት የሌለዉ አካሄዶች በክልሉ እየታዩ ነው" ብለዋል።
ክልሉ መልሶ ወደ ግጭት እንዳይገባ ስጋት መኖሩን የገለጹት አቶ መብሪህ፤ ይህንን ስጋት ከሚጨምሩ አካሄዶች ሁሉም አካላት ሕዝብን ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
"የትግራይ ክልል አስከፊ ከሚባል ጦርነት እንደመውጣቱና ክልሉ አሁንም ከፍተኛ ችግር ባለበት ሁኔታ ወደ ግጭት እንዳያመራ ሕዝቡ ከዚህ ዓይነት ግጭት ቀስቃሽ አካላት መራቅ አለበት" ብለዋል።
"የትግራይ ሕዝብ ይህንን ሁኔታ በደንብ ይገነዘባል" ሲሉ የገለጹት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ "ካለፈዉ ግጭት በመማር ሕዝቡ 'በቃችሁ' ሊላቸው ይገባል" ሲሉም ለአሐዱ ተናግረዋል።
የወታደራዊ አዛዦች መግለጫን ተከትሎ በትግራይ ዳግም ከፍተኛ ውጥረት የተከሰተ ሲሆን፤ በዶክተር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ህወሓት ምንም እንኳን በጊዜያዊ አስተዳደሩ እና በክልሉ ፖሊስ ክልከላ ቢደረግበትም በትላትናው ዕለት እሁድ ረፋድ ላይ የጦር አዛዦችን ሀሳብ የሚደግፍ ሰልፍ በመቀሌ ከተማ ሐዉልቲ ሰማዕታት ግቢ ውስጥ እና ውቅሮን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች አካሂዷል።
በተመሳሳይ ቅዳሜ ዕለት ደግሞ የጦር አዛዦችን ውሳኔ የሚቃወም በጊዜያዊ አስተዳደር የተጠራ ሰላማዊ ሰልፍ በመኾኒ ከተማ መካሂዱም የሚታወስ ሲሆን፤ በትላትናው ዕለትም ይሄንኑ ውሳኔ የሚቃወም ሰልፍ በአዲግራት ተካሂዷል።
የትግራይ ክልል አስከፊ ከሆነ ጦርነት ለመዉጣት ጥረት ላይ ያለ ክልል ቢሆንም፤ በድህረ ጦርነት ያሉ ችግሮች ሳይፈቱ ዳግም ውጥረት ውስጥ መግባቱ ትኩረት ሊሰጠዉ የሚገባዉ ጉዳይ መሆኑ ተገልጿል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ