ጥር 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት 6ኛ ዙር ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 15ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡
በዚህ ጉባኤም የፌደራል ዳኞች አስተዳዳር ጉባኤ ሁለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ላይ ያቀረበውን የስንበት ውሳኔ አስመልክቶ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ አፅድቋል፡፡
በዚህም መሠረት አዱኛ ነጋሳ እና አክሊሉ ዘሪሁን የተባሉ ሁለት የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች "በሙስና እና በብልሹ አሰራር ላይ ተገኝተዋል" ያላቸውን ዳኞች እንዲሰናበቱ አድርጓቸዋል፡፡
ዳኞቹም የፌደራል ዳኞች አስተዳዳር ጉባኤ በከባድ ዲሲፒሊን ክስ መስርቶባቸው ከዳኝነት ሥራቸው እነዲሰናበቱ በቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እፀገነት መንግስቱ ሪፖርት ቀርቧል፡፡
ሁለቱ ዳኞች በሥራ ላይ በነበሩ ጊዜ ሀላፊነታቸውን ያላግባባ በመጠቀማቸው ዳኛ አደኛ ነጋሳ ሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወር እንዲሁም ዳኛ አክሊሉ ዘሪሁን በ1 ዓመት ከስድስት ወራት እንዲቀጡ አድርጓል፡፡
ቋሚ ኮሚቴውን የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ ተቀብሎ ከመረመረ በኃላ፤ በዳኞቹ ላይ የተወሰደው እርምጃ ተገቢ ሆኖ በማግኘቱ ከዳኝነት እንዲሰናበቱ በምክር ቤቱ ውይይት ተካሂዶበት ውሳኔ ተሰጥቶበታል፡፡
በመሆኑም ምክር ቤቱ በፌደራል ዳኞች ጉባኤ የቀረበለትን የሁለት ዳኞች ከዳኝነት እንዲሰናበቱ የሚል ጥያቄ፤ በሁለት ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጭ ድምፅ አፅድቆታል፡፡