ጥር 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በኢስላማዊ አለባበስ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ስለሚጉላሉ ተማሪዎች አስመልክቶ፤ የመጨረሻ ያለውን ደብዳቤ ለትምህርት ሚኒስቴር መፃፉን አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ ምክር ቤቱ ከኢስላማዊ አለባበስ ጋር በተያያዘ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች የሚደርስባቸውን ከፍተኛ ጫናና ከትምህርት መፈናቀል በዘላቂነት መፍትሄ እንዲያገኝ ውይይቶች ማድረጉን የገለጸ ሲሆን፤ በዚህ ወር ብቻ ሦስት ጊዜ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ደብዳቤ ቢጽፍም እስከ አሁን ተገቢ ምላሽ ማግኘት አለመቻሉን ገልጿል፡፡
ነገር ግን አሁንም በኢስላማዊ አለባበስ ብቻ መስሊሞችን ከትምህርት ገበታቸው ማፈናቀል አካባቢውን እየቀያየረ መቀጠሉን በደብዳቤው የገለጸ ሲሆን፤ ችግሩ በዲላ ዩንቨርስቲ ሙስሊም ተማሪዎች ላይ መፈፀሙን ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በደረሰው መረጃ ለማወቅ መቻሉን አመላክቷል፡፡
በመሆኑም እነኚህ ከየትኛውም አይነት ጫና ነፃ ሆነ ትምህርት የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ተገፎ ከትምህርት ገበታቸው በኃይል እንዲነጠሉና ወደ ዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢው እንዳይገቡ የተከለከሉ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በአፋጣኝ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ጠይቋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴርም "አስተዳደራዊ ትዕዛዝ እንዲሰጥና በሀገር አቀፍ ደረጃ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያስቀምጥ ለመጨረሻ ጊዜ እንጠይቃለን" ሲል ምክር ቤቱ በደብዳቤው አሳስቧል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ