ጥር 15/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሶማሊያዊ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ ከግብጽ አቻቸው አብደል ፈታህ ኢልሲሲ ጋር የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ውይይት ለማድረግ ካይሮ መግባታቸው ተነግሯል፡፡
መሪዎቹ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የጋራ ጥረቶችን በማጠናከር፣ በጸጥታ ዘርፍ ትብብርን bማፋጠን እንዲሁም በቀጠናው ሰላም ዙሪያ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሶማሊያ የዜና ወኪሎች የጉብኝት ግብዣው የመጣው፤ "ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የጋራ ጥረቶችን ማጠናከር እና በጸጥታ እና በአካባቢው ሰላም መስኮች ትብብርን ማፋጠን" ላይ ለመወያየት በግብፅ ፕሬዝዳንት በኩል መሆኑን ዘግበዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ለኢኮኖሚያዊ እና ልማታዊ ትብብር እድሎች ቅድሚያ እንደሚሰጡ አፅንዖት ተሰጥቷል፡፡
ባለፈው ነሃሴ ወር ላይ ሀሰን ሼክ መሃሙድ ለሁለት ቀናት በካይሮ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት፤ ግብፅ እና ሶማሊያ የሁለትዮሽ የጸጥታ ትብብርን ለማጠናከር የመከላከያ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2024 የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ መጠን 59 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል ተብሏል፡፡
በዛሬው ዕለት ደግሞ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ ኤል ሲሲ የሶማሊያ አቻቸውን ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድን በካይሮ ተቀብለው የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በማሳደግ እና በቀጠናዊ ጉዳዮች ይወያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ባለፈው አንድ ዓመት ግብፅ እና ሶማሊያ በኢኮኖሚ፣ በትምህርት፣ በጸጥታ እና በወታደራዊ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር የሁለትዮሽ የከፍተኛ ደረጃ ጉብኝቶችን ተለዋውጠዋል።
ፕሬዝዳንት ኢልሲሲ "ግብፅ ሶማሊያን በሁለትዮሽ ትብብርም ሆነ በሶማሊያ ጥያቄ በአፍሪካ ህብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ በመሳተፍ የሶማሊያን ፀጥታና መረጋጋትን ለማስፈን በትኩረት እየሰራች ነው" ብለዋል።
ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል እየተካሄደ ያለው ግልጽ ያልሆነ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ ነው እየተነገረ የሚገኘው፡፡
ግብፅ የሶማሊያን የደህንነት ተግዳሮቶች ለመፍታት እና አገራዊ ተቋሞቿን ለማጠናከር ያላትን የቴክኒክ ድጋፍ እና ሙያዊ ድጋፍ ለመስጠት ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች።
ካይሮ የሶማሊያ መንግሥት ፀጥታን ለማስፈን፣ ሽብርተኝነትን ለመከላከል እና በግዛቷ ውስጥ ያለውን የመንግሥት ሉዓላዊነት ለማስከበር ድጋፍ እንደምታደርግ ደጋግማ ገልጻለች።
በፈረንጆቹ 2024 በኢትዮጵያ እና በሶማሌላንድ መካከል በተደረገው ስምምነት ላይ፤ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል በተፈጠረው ውዝግብ ውስጥ ግብፅ ለሶማሊያ አንድነት እና የግዛት አንድነት የማያቋርጥ ድጋፍ ስታቀርብ ቆይታለች።
ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ ዕውቅና እንድትሰጥ በምትኩ የባህር በርና የጦር ሰፈር መገንቢያ ማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ፤ ሶማሊያ "የሉዓላዊ መብቴን የሚጋፋ ነው" በማለት አጥብቃ ተቃውማ ነበር፡፡
ነገር ግን እራሷን እንደ ሀገር በምትቆጥረው ሶማሊያላንድና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገው የሰጥቶ መቀበል ሰምምነት፤ በምን እንደተቋጨ ባይታወቅም፤ "ሉዓላዊነቴ ተደፍሯል" በሚል ለ11 ወራት ያህል ኢትዮጵያን ስትከስ የቆየችው ሶማሊያ፤ በአንካራ አደራደሪነት ፖለቲካዊ መፍተሄ ለማምጣት ስምምነት አድረገዋል፡፡
ይህን ደግሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ሆኑ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ ስምምነቱን መቀበላቸውን በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ቢሆንም ግን ኢትዮጵያ በቀጠናው ሊመጡ የሚችሉ የትኞቹንም ፖለቲካዊ ጫናዎች በትኩረት በመከታተል አኳያ ለአፍታ እንኳን የምትዘነጋው ጉዳይ መሆን እንደሌለበት፤ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይስተዋላል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ